ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ከ117 ሚልየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውና 972 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አራት የመስኖ ካናል ግንባታ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል

ጅግጅጋ ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦  በሶማሌ ክልል ከ117 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውና 972 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አራት የመስኖ ካናል ግንባታዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። 

የመስኖ ካናሎቹ በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ  ምትኩ አየለ (ዶ/ር)፣ የሶማሌ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ኢማን (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ። 

የክልሉ የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ  አብዱቃድር ኢማን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት በክልሉ እያደገ የመጣውን የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ  ጥገኝነት ለማላቀቅ  እና የመስኖ ልማት ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። 



ፕሮጀክቶቹ  ለአካባቢው ከፊል አርብቶ አደሮች የበጋ ልማትን እንዲያከናውኑ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩት አብዱቃድር(ዶ/ር)፤ ህብረተሰቡ በተፈጠረለት እድል በመጠቀም በምግብ ራሱን እንዲችሉ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በቀጣይነት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

በፌዴራል የግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ በተገነባው የአነስተኛ የመስኖ ግድብና ካናሎቹን የአካባቢው ህብረተሰብ በአግባቡ በመጠቀም  የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባሻገር የሚያመርተውን ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ  እንዲሆን ያስችላል ብለዋል። 

በክልሉ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋምና የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ  ካናል ግንባታዎች በስፋት በማካሄድ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። 

በአፍዴ፣ ዳዋና ሸበሌ ዞኖች ከሚገኙ ወረዳዎች ዋቢ ሸበሌ፣ ዳዋና ሌሎች ወንዞችን በመጥለፍ በአባቆሩ፣ ኢሜ፣ ኤልከሬና ኤልመዶው የተገነቡ የመስኖ ካናሎቹ 117 ሚሊዮን ብር እንደወጣባቸውና 972 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። 



በምረቃው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ምትኩ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት የእርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

በሶማሌ ክልል እየተከናወኑ ያሉ አነስተኛ የካናል ግንባታ ፕሮጀክቶች የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚኒስቴሩና ክልሉ የተያዘው የተቀናጀ ጥረት አካል ነው ብለዋል፡፡ 

የአካባቢው ህብረተሰብ በበኩላቸው በፌዴራል የግብርና ሚኒስቴር በተከናወነላቸው የአነስተኛ መስኖ ካናል ፕሮጀክት መደሰታቸውን ገልፀዋል። 

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከዚያም ከፍ ሲል ምርታማነታቸውን በማሳደግ በምርት አቅርቦት ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከመስኖ ካናሉ ግንባታ ጎን ለጎን ቀደም ብለው የማልማት ስራ እንደጀመሩም ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም