ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ውብና ማራኪ ከተሞች እንዲፈጠሩ እያገዘ ነው - የናፍቆት ድሬዳዋ በዓል ተሳታፊዎች

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ውብና ማራኪ ከተሞች እንዲፈጠሩ እያገዘ መሆኑን አስተውለናል ሲሉ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የናፍቆት ድሬዳዋ በዓል ተሳታፊዎች ተናገሩ።

ሶስተኛ ቀኑን በያዘው የናፍቆት ድሬዳዋ በዓል ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ዛሬ በቀድሞው የድሬዳዋ የምድር ባቡር ጣቢያ ግቢ ውስጥ የተለያዩ ችግኞች በመትከል በዓሉን አክብረዋል።

ከኢትዮጵያዊያን ወላጆቹ ጋር በዓሉን እያከበረ የሚገኘው የሁለተኛው ትውልድ አካል የሆነው ካናዳዊው ወጣት አህመድ አደም እንዳለው በበዓሉ ላይ መሳተፉ ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማወቅ እና ከወላጆቹ የትውልድ ከተማ ጋር ለመተሳሰር ዕድል እንደፈጠረለት ተናግሯል።

ችግኝ መትከልና ተንከባክቦ ማሳደግ ለም እና ውብ የመኖሪያ ከተማ ለመፍጠር አስችሏል ሲልም ይናገራል።

እሱም ከወላጆቹ  አገር እና ከተማ  ጋር  ያለውን ትስስር ለማጠናከር ችግኝ በመትከል  አሻራውን ማሳረፉን በመግለፅ።


 

ከሲዊድን የመጡት  አቶ አህመድ ዑመር እና ወይዘሮ ሳአዳ መሐመድ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በአገር ደረጃ በተቀናጀ መንገድ መተግበሩ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም በግብርናም ሆነ በኢንዱስትሪው የተሻለ ውጤት ለማምጣት መሠረት እየጣለ ይገኛል ብለዋል።

አቶ ዑመር አክለውም በአረንጓዴ አሻራ የተከናወኑት ስራዎች ከተሞችን ውብና ተስማሚ አየር ያላቸው እንዲሆኑ ማገዙን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ገልፀዋል።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራ ተሳታፊ በመሆናቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በድሬዳዋ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የቱሪዝም ሀብቶቿን ለመጡበት አገር በስፋት እንደሚያስተዋውቁ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአገራችንን ከተሞች ውብና ማራኪ የመኖሪያ ስፍራ እንዲሆኑ ሚናው የጎላ መሆኑን አስተውያለሁ ያሉት ደግሞ ለበዓሉ ከቢሾፍቱ ከተማ የመጡት አቶ ሣህለ ኢድሪስ ናቸው።


 

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ህይወትን ማስቀጠል እና የተሻለች አገር ለትውልድ ማስተላለፍ ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ፤ የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ሁለንተናዊ ተስስር እያጠናከረ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው በዓል እነዚህን ጅምር እንቅስቃሴዎች ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳለው በመጥቀስ።

ዛሬ በቀድሞ የድሬዳዋ ምድር ባቡር በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ተሳታፊ ሆነዋል።

የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ዓመታዊ በዓል ነገም በልማት ስራዎች ጉብኝት እና ለእንግዶቹ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ውይይት በማድረግ ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም