ቀጥታ፡

በክልሉ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በስኬት ተጠናቋል - ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው

አሶሳ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ገለጹ።

በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ይፋዊ ማጠቃለያ ፕሮግራም ሲካሄድ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በሰጡት መግለጫ በክልሉ ለአንድ ሳምንት የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ዛሬ በስኬት ተጠናቋል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሁሉንም የክልሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት በሚገባ ለማሳተፍ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

ተሳታፊዎችም በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት እና ተቆርቋሪነት አጀንዳ ማሰባሰቡን ማከናወናቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።


 

ይህም እንደ ሀገር የሚያኮራ እና ኮሚሽኑ ለጀመረው ጥረት ስኬታማነት እጅግ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ስኬታማነት ከኮሚሽኑ ሠራተኞች ጥረት ባሻገር የክልሉ መንግስት፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የጸጥታ አስከባሪ አካላት እና ሌሎችም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ዘገየ በክልሉ ለተከናወነው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ስኬታማነት ትብብር ያደረጉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም