በበጀት ዓመቱ ለ345 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ለ345 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ345 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በቅርቡ የተደረገው የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ሪፎርም ለዜጎች አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሁም ደኅንነታቸው፣ መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ በውጭ አገራት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አግዟል።
ከመዳረሻ አገራት ጋር የሚደረግ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የዜጎችን ደኅንነትና መብት በማስጠበቅ መልካም የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረጉም ይታወቃል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት አስተባባሪ ብርሃኑ አለቃ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዜጎች በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ደኅንነታቸው፣ ጥቅማቸውና መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።
የውጭ አገር ሥራ ሥምሪቱ በሕጋዊ መንገድ መሆኑና ከመዳረሻ አገራት ጋር ያለው ስምምነት ወደ ውጭ አገር ለሥራ ይሄዱ የነበሩ ዜጎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ማደጉን ገልፀዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ለ345 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
የሥራ ስምሪቱ ዜጎች ደህንነታቸው፣ የሚያገኙት ጥቅምና መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ በሚያስችል መልኩ መከናወኑንም አብራርተዋል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ በተለይም ከፍተኛ የሰው ቁጥር የሚሄድባቸውን አካባቢዎች በጥናት በመለየት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እራሳቸውን ከሚሰሩት ሥራ ጋር እንዲያላምዱ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አቶ ብርሃኑ አስገንዝበዋል።
ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ በመሰማራታቸውም የተፈላጊነታቸው ቁጥር እየበዛ መጥቷል፤ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ አራት የነበረውን የውጭ አገር የመዳረሻ ቁጥር ወደ ሰባት ለማስፋት ስምምነት መደረጉን ገልፀዋል።
ተቋሙ አሠራሩን በማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘና የዜጎች ደኅንነት ተጠብቆ ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ ዜጎችን ከሚያዘዋውሩ ደላሎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።