ቀጥታ፡

10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባዔ በብሪክስ አባል አገራት ወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2016 (ኢዜአ)፦10ኛው የብሪክስ ወጣቶች ጉባዔ  በአባል አገራቱ ወጣቶች መካከል  ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር የከፈተ እንደነበር የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋዓድ ገና የተመራ ልዑክ ቡድን ከቀናት በፊት በሩስያ ኡልያኖስክ በተካሄደው 10ኛው የብሪክስ የወጣቶች ጉባዔ ተሳትፏል። 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋዓድ ገና፤ ኢትዮጵያ በጉባዔው የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።  

በመግለጫውም፤ በጉባዔው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሁሉም የብሪክስ አባል አገራት የተወከሉ የወጣት አመራሮችና ሚኒስትሮች መሳተፋቸውን ገልጿል።

ኢትዮጵያም የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏን ተከትሎ በጉባዔው ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏን ተናግሯል።

በትምህርትና ሥልጠና፣ ሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በጤና፣ በስፖርትና በኪነ-ጥበብ ዙሪያ ላይ ጉባዔው መምከሩን ጠቁሟል።

ጉባዔው የአባል አገራቱን ወጣቶች በአንድ መድረክ በማሰባሰብ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲመክሩና በመፃዒ ዕድላቸው ዙሪያ እንዲወያዩ በር ከፍቷል ነው ያለው።

ወጣቶች በየአገራቸው ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ መደላደልን የፈጠረ መድረክ መሆኑንም ጠቅሷል። 

ጉባዔው በአጠቃላይ በብሪክስ አባል አገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር በር የከፈተ እንደነበር የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወጣት ፉአድ ገና ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም