ቀጥታ፡

የወንጀል መከላከል፣ የምርመራና የመረጃ አሰባሰብ አሰራሮችን  በቴክኖሎጂ በታገዘ  መንገድ እየተከናወነ  ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦የወንጀል መከላከል፣ የምርመራና የመረጃ አሰባሰብ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። 

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ሙሊሳ አብዲሳ፤ በወንጀል መከላከልና በምርመራ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በወንጀል ምርመራና በመከላከል ረገድም በቴክኖሎጂ የተደገፉ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራሮች በስፋት እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የፖሊስና ህብረተሰቡ የወንጀል መከላከል ጠንካራ ቁርኝትም ሌላ ተጨማሪ እድል መሆኑን ጠቅሰው በዚሁ ቅንጅታዊ አሰራር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተለያዩ የወንጀል ሙከራዎችን በማክሸፍ አጥፊዎችንም በፍጥነት በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ማቀረብ የተቻለው በፖሊስና ህብረተሰቡ የተባበረ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

በወንጀል መከላከል፣በምርመራና በመረጃ አሰባሰብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች በስፋት እየተተገበሩ መሆኑም የፖሊስን አሰራር ፈጣንና ዘመናዊ አድርጎታል ብለዋል።

በቀጣይነትም የፖሊስን አሰራር ይበልጥ የማዘመን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የሕብረተሰቡም ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በወንጀል ተግባር ላይ የሚሰማሩ አካላትን በቁጥጥር ስር አውሎ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም ሃላፊው አረጋግጠዋል።

በሃሳብ የበላይነት በውይይትና በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም