ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠናከር አለበት

 አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016 (ኢዜአ):- በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና ተናገሩ። 

በሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው "ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት" ለመከላከያ ሰራዊት የኮምፒውተርና ሌሎች ግብዓቶችን አበርክቷል። 

ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የራሱ ግልጽ የሆነ መሥመር የተቀመጠለት የመላ ኢትዮጵያውያን የመጨረሻ ምሽግ ነው። 

ይህንን በመገንዘብ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ያሳዩት ድጋፍ ለሰራዊቱ የሞራል ስንቅ ነው ብለዋል። 

በቀጣይም በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ለሠራዊቱ ድጋፍ በማድረግ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት።   

የኢትዮጵያን ህልውና ማረጋገጥ የዜጎችን ህልውና ማስጠበቅ መሆኑን የገለጹት ጄኔራል ጌታቸው፤ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ሁሌም ወጥ አቋም ሊኖር ይገባል ብለዋል። 

ጽንፈኛ ቡድኖች ሰራዊቱን ያልተገባ ሥም ቢሰጡትም ሠራዊቱ አገር የመጠበቅ ተልዕኮውን ለአፍታም እንደማይዘነጋ ተናግረዋል። 

በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሰራዊቱ የተገነባበትን አገራዊ እሴት በውል መረዳት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል። 


 

በሰሜን አሜሪካ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት ፕሬዝዳንት ጋሻው ቢርቦ፤ የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያን ከመፍረስ ሕዝቦቿን ከመበተን ያዳነ ሰራዊት ነው ብለዋል።

ከሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያ የመጣንበት ምክንያትም የጋራ አገራችንን ለመጠበቅ ሌት ተቀን ለሚደክመውና የህይወት መስዋዕትነት ለሚከፍለው ለመከላከያ ሰራዊት ክብር ለመስጠት ነው ሲሉም ተናግረዋል።  


 

የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሰላም ዋቆ፤ መከላከያ ከሌለ የአገርን ዳር ድንበር የሚጠብቅ እንደሌለ መረዳት ይገባናል ብለዋል። 

የመከላከያ ሰራዊት ከሌለ እኛም የለንም ያሉት ኃላፊዋ፤ የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍለውን ሰራዊት ከጎኑ ሆኖ ማገዝ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

የድርጅቱ ፕሬዝዳንትና አባላት ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በመሆን በመከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም