የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በእቅዱ መሰረት ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
አየር መንገዱ የ2016 ዓ. ም. ዓመታዊ አፈጻጸም ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በሰጡት ማብራሪያ፤ አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ ስኬታማ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አጠቃላይ 577 ሺህ 746 የበረራ ሰዓት ማስመዝገቡን ጠቅሰው ይህም ከአምናው የበረራ ሰዓት ጋር ሲነጻጸርም የ19 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙን በማስታወቅ ይህም ከአምናው ጋር ሲወዳደር የ23 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አንስተዋል።
በዚህም ግሩፑ በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 02 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና የተገኘው ገቢ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ አየር መንገዱ ካስመዘገበው አመታዊ ገቢ 5 ቢሊዮን ዶላሩ የተገኘው መንገደኞች በማጓጓዝ መሆኑን አብራርተዋል።
የተገኘው ውጤትም አየር መንገዱ በእቅዱ መሰረት እድገቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በካርጎ ጭነት አገልግሎት በተጠናቀቀው በጀት አመት 754 ሺህ 681 ቶን ማጓጓዙን በማንሳት ይህም ከአምናው ጋር ሲወዳደር የስድስት በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከጭነት አገልግሎት አየር መንገዱ 1 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አብራርተዋል።
አየር መንገዱ በርካታ የካፒታል ፕሮጀክቶችን እያሰራ እንደሚገኝ በማስታወቅ 458 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ስራ ላይ መሆናቸውን በአብነት አንስተዋል።
አየር መንገዱ ከራዕይ 2035 ጋር በማሰናሰል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በማንሳት በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም 105 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
እንዲሁም ቀደም ሲል ትዕዛዝ ላይ ካሉት አውሮፕላኖች ጋር በድምሩ125 አውሮፕላኖች በትዕዛዝ ላይ መሆናቸውንና እ.አ.አ ከ2027 እስከ 2030 አውሮፕላኖቹን ለመረከብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣የኢ-ኮሜርስ ፋሲሊቲ፣የራሱን የሃይል መቆጣጠሪያ ሰብ ስቴሽን ፣የቦሌ አዲስ አበባ የሀገር ውስጥ ተርሚናል ማስፋፊያና ሌሎች በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በበጀት ዓመቱ አምስት ዓለም አቀፍ የመንገደኛ መዳረሻዎችን በመጨመር የዓለም አቀፍ በረራ መዳረሻዎቹን ማሳደጉን ተናግረዋል።
በዚህም ወደ እንግሊዝ ጋት ዊክ ፣ስፔን ማድሪድ ፣ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጉይ፣ ሴራሊዮን ፍሪታውንና ፣ቦትስዋና ማዊ ዓለም አቀፍ ከተሞች አየር መንገዱ በረራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ይህም አየር መንገዱ የነበሩትን ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ወደ 139 ከፍ ለማድረግ እንዳስቻለው ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በሀገር ውስጥ ወደ ደምቢ ዶሎ ፣ ነቀምትና አክሱም የተጀመሩት በረራዎች በ2016 በጀት አመት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዬን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።