በአፍሪካ የነፃነት ትግልና የሰላም ግንባታ ሂደት የኢትዮጵያ ሚና የላቀ ነው- የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመከላከያ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የነፃነት ትግልና የሰላም ግንባታ ሂደት የኢትዮጵያ ሚና የላቀ ነው- የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመከላከያ መኮንኖች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የነፃነት ትግልና የሰላም ግንባታ ሂደት የኢትዮጵያ ሚና የላቀ መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመከላከያ መኮንኖች ገለጹ።
የኢፌዴሪ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በአጭርና በረጅም ኮርስ ከመደበኛ እስከ 2ኛ ዲግሪ ወታደራዊ የደህንነትና ስትራቴጂካዊ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች አስመርቋል።
በኮሌጁ ከኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖች በተጨማሪ የስድስት የተለያዩ ጎረቤት አገራት ወታደራዊ መኮንኖችም ሰልጥነው ተመርቀዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የኬንያ ሪፐብሊክ አየር ኃይል ባልደረባ ብርጋዴር ጄኔራል ኦሳልድ ኦዱር፤ በአስር ወራት የኮሌጁ ቆይታቸው ባገኙት የላቀ ወታደራዊ ትምህርት መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን ጨምሮ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ስጋቶችን በትብብር ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና መጋራታቸውንም አንስተዋል።
የአፍሪካን አህጉራዊ ቀጣና ትብብር በማጠናከር አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥም ሁነኛ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
አፍሪካዊያን በጋራ ለሰላምና ነፃነታቸው እንዲታገሉ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የመሪነት ሚና በመጫዎት ያበረከቱትን የላቀ አስተዋጽኦም አስታውሰዋል።
በመሆኑም በስልጠና ቆይታችን በዓድዋ ተራሮች የነፃነት ተጋድሎ የኢትዮጵያዊያንን የማሸነፍ ጥበብና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ድል በአግባቡ የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።
በአፍሪካ የነፃነት ትግልና የሰላም ግንባታ ሂደት የኢትዮጵያ ሚና የላቀ መሆኑን አንስተው አሁንም መቀጠሉን ተናግረዋል።
የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ኮሎኔል ማንጎንግ አንይጆኝ፤ በኮሌጁ ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና ተግባር የተደገፈ ወታደራዊ ዕውቀት መቅሰማቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በስትራቴጂክ የትምህርት አይነት ያገኙት ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ዕውቀት ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በአህጉሪቷን የቅኝ ግዛት ተጋድሎ ወቅትም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ኔልሰን ማንደሌላ፣ ኩዋሜ ኑኩርማን ጨምሮ ለአፍሪካ መሪዎች የሰጡት ድጋፍ በታሪክ የሚታወስ መሆኑን አስረድተዋል።
በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና ከጥንት እስካሁንም እያበረከተችው ላለው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የሶማሌ ላንድ ሪፐብሊክ የብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ኮሎኔል አሕመድ ኤይድድ፤ በመከላከያ ዋር ኮሌጅ የደኅንነትና ስትራቴጂካዊ የትምህርት ቆይታቸው ብዙ እውቀት ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ዋር ኮሌጁ ላመቻቹላቸው የትምህርት ዕድል ምስጋና አቅርበዋል።
በዘርፉ የትምህርት እድል ከማመቻቸት ባለፈ በቀጣናው ሽብርተኞችን በመዋጋት ረገድ የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ወታደራዊ አታሼዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን በትምህርት ቆይታቸው አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ መኮንኖች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።