የሉሲ ቅሪተ አካል ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ያበሰረ ነው - አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ ቅሪተ አካል ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ያበሰረ ነው - አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ያበሰረ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
የሉሲ ቅሪተ አካል በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ህዳር 24 ቀን 1974 በአፋር ክልል ሀዳር የተባለ ቦታ መገኘቱ ይታወቃል።
“የድንቅ ግኝት ግማሽ ምዕተ ዓመት” በሚል መሪ ሃሳብ የድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ በኢትዮጵያ ከ7 ሚሊየን አመት ጀምሮ እስከ 200 ሺህ አመት ድረስ የሰው ዘር ቅሪተ አካል መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት በፊት ምደር ላይ መኖሯ የተረጋገጠው የሉሲ ቅሪተ አካል መገኘት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ያበሰረና የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናትን የትኩረት መስክ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመሆኑም የዚሁ ታሪካዊ ክስተት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮበልዩ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚከበርበት ሁነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በይፋ ተበስሯል ብለዋል።
የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ አመት የወርቅ እዮቤልዩ መታሰቢያ በተለያዩ መልኩ ማክበር ያስፈለገበት ዋነኛ ዓላማም ኢትዮጵያ እውነተኛ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለዓለም ለማስተዋወቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት የሚያስረዱ በርካታ ግኝቶች መኖራቸውን በማስረጃ አስደግፎ ማሳየት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የሉሲ መታሰቢያ በቀጣይነት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች መከበሩ የሚቀጥል መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የሉሲ ቅሪተ አካልን ያገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡ ሌሎች የዘርፉ ምሁራን ታድመዋል፡፡