ቀጥታ፡

የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሰብሉ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በሽታዎችን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል-የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሰብሉ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎችን አቀናጅቶ መቀጠል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ። 

ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ ላይ ያተኮረ ለሁለት ቀናት የሚቆይ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

አውደ ጥናቱ የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች፣ በእፅዋት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል ። 

አውደ ጥናቱ በአገሪቱ በስፋት እየተመረተ ያለውን የስንዴ ምርትና ምርታማነት ሊቀንስ በሚችለውና በፈንገስ ምክንያት የሚመጣውን የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚመክር መሆኑ ተጠቁሟል።  

በአውደ ጥናቱ 13 ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን እስካሁን በበሽታው ዙሪያ የተሰሩ የምርምር ውጤቶችን በመገምገም በአገሪቱ ያሉ ክፍተቶች የሚለዩበት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዲሪባ ገለቲ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት የስንዴ በሽታ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን በተለይ ይህኛው በሽታ የስንዴውን ራስ የሚያጠቃ ነው።

በሽታው በአየር ንብረት ሁኔታ የሚወሰን መሆኑን አንስተው ከፍተኛ ዝናብና ሙቀት ባለበት ወቅት የሚያደርሰው ተፅዕኖ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ።

በሽታው በአንድ ማሳ ላይ ሰብልን አፈራርቆ ባለመዝራትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰትና የስንዴን ምርታማነት የሚቀንስ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

 ኢንስቲትዩቱ በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቆጣጠር በሽታው በየት አካባቢና በምን ደረጃ እየተከሰተ መሆኑን የሚያሳይ ቅኝት የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በምርምር በሽታውን የሚቋቋም ዝርያ የማሻሻልና የሰብል አያያዝ ስልቶችን እያከናወነ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሽታውን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በማውጣትና መነሻ ዘር በማዘጋጀት የማሰራጨት ስራ እንዲሁም አርሶ አደሩንና የልማት ሰራተኛውን ስለበሽታው የማስገንዘብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መድረኩ የሚመለከታቸው አካላት በሽታው እያደረሰ ያለውን ጉዳት ተገንዝበው ጉዳቱን ለመቋቋም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስገንዘብ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልፀዋል። 

በሽታው የሰብል ጥራትን የሚቀንስና ከሰብሉ የሚዘጋጁ የምግብ ምርቶች ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ጉዳቱን ለመቀነስ የምርምና የትምህርት ማዕከላት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በቅንጅት ሊረባረቡ ይገባል ነው ያሉት።

አርሶአደሩ በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም የሚደረግለትን የቴክኒክ እገዛ በመተግበር ተፅዕኖውን ለመቀነስ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በኢንስቲትዩቱ የእፅዕዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ነፃነት ባጫ(ዶ/ር) በበኩላቸው የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከሰተ ቢሆንም በቅርብ ዓመታት የስንዴ ምርት እድገትን ተከትሎ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረዋል። 

በምርምር ተቋማት በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱም በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መድኃኒቶች፣ በሽታውን ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችንና የተቀናጀ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎችን በመለየት  ለአርሶ አደሩ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል። 

አውደጥናቱ በምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ ተመሳሳይ ስራዎችን ለመቃኘትና ክፍተቶችን ለመለየት ብሎም አለምአቀፍ ልምዶችን በመውሰድ አቅጣጫ የሚወሰድበት መሆኑን ገልፀዋል።  

የስንዴ ምርት በስፋት እየተመረተ ቢሆንም ከአለም አንፃር ሲታይ አሁንም የሚቀር ስራ ስላለ ባለን አቅም ልክ ለማምረት ምርት የሚቀንሱ በሽታዎችና ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም በትብብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል። 

 

 

 

 

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም