በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል - የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል - የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን
አሶሳ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በ2016 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መለሰ ኪዊ በሰጡት መግለጫ እንደጠቀሱት፤ በክልሉ ከቀጥተኛ ታክስ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ የታክስ ዓይነቶች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን፣ ታክስ ካልሆኑ 357 ሚሊዮን፣ እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 148 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል፡፡
በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደው ባለስልጣኑ የዕቅዱን 95 በመቶ ማሳካት እንደቻለም ገልፀዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 0 ነጥብ 6 በመቶ ወይም የ22 ሺህ 530 ብር ብልጫ እንዳለውም አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡
የግብር ከፋዩ ግንዛቤ እያደገ መምጣት በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉንም ገልፀዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች የባለሃብቶች በታሰበው ጊዜ ወደ ስራ አለመግባት ገቢውን ለመሰብሰብ ተግዳሮት እንደነበርም አቶ መለሰ ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ እንደያዘም በወቅቱ ተገልጿል።