የሉሲ ቅሪተ አካል ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነትን በማረጋገጥ የሰው ዘር ጥናት ማዕከል እንድትሆን አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ ቅሪተ አካል ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነትን በማረጋገጥ የሰው ዘር ጥናት ማዕከል እንድትሆን አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦የሉሲ ቅሪተ አካል ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነትን በማረጋገጥ የሰው ዘር ጥናትና ምርምር ማዕከል እንድትሆን አስችሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
“የድንቅ ግኝት ግማሽ ምዕተ ዓመት” በሚል መሪ ሃሳብ የድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመት በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የሉሲ ቅሪተ አካልን ያገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡ ሌሎች የዘርፉ ምሁራን ታድመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ድንቅ ባህላዊ፡ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡
የሉሲ ግኝት የሳይንሱ ማኅበረሰብ ስለ ምድርና በውስጧ ስላለው የህይወት መልክ ለማወቅ ያስቻለ ሁነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለበርካታ የምርምር ስራዎች መሰረት የጣሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ባሻገር አፍሪካ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን እውቅና የሰጠ ስለመሆኑ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሳይንስ የሰው ልጅ በምድር መኖር ከጀመረ ስድስት ሚሊዮን ዓመታትን እንዳሳለፈ እንደሚያስረዳ ጠቅሰው፤ በዘርፉ በተደረጉ የሳይንስና ምርምር ተግባራትም ኢትዮጵያ ቁልፍ ቦታ እንዳላት ተናግረዋል፡፡
በዓለም ላይ ከተገኙ 22 ቅሪተ አካላት መካካል አስራ ሶስቱ የተገኙት በኢትዮጵያ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
ከቅሪተ አካላት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የተገኙ ጥንታዊ መገልገያ መሳሪያዎች የቀደመ ዘመን የቴክኖሎጂና ባህል መገኛ መሆኗን እንደሚያመላክቱም አብራርተዋል፡፡
መንግስት ባለፉት ዓምስት ዓመታት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት ወደ ልማት ጥቅም ላይ ለማዋል በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ የተከናወኑ ስራዎችንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
እነዚህ የቱሪዝም ልማት ስራዎችም የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተስማሙ መሆናቸውን ጠቅሰው መሰል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በመላው ዓለም የሚኖሩ ድንቅ የሆነችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡