የሉሲ /ድንቅነሽ/ ግኝት ለሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት መለኪያ እና ማጣቀሻ ነው - ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ /ድንቅነሽ/ ግኝት ለሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት መለኪያ እና ማጣቀሻ ነው - ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ የሉሲ /ድንቅነሽ/ ግኝት ለሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት መለኪያ እና ማጣቀሻ መሆኑን አሜሪካዊው ፓሌዮአንትሮፖሎጂስት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን ገለጹ።
“የድንቅ ግኝት ግማሽ ምዕተ ዓመት” በሚል መሪ ሃሳብ የድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመት በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የሉሲ ቅሪተ አካልን ያገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡ የዘርፉ ምሁራን ታድመዋል፡፡
የሉሲን ቅሪተ አካል ያገኙት አሜሪካዊው ፓሌዮአንትሮፖሎጂስት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በብዙ ምክንያቶች የምትደነቅ አገር ናት።
በተለይም እንዴት ሰው ሆንን የሚለውን በአግባቡ እንድንረዳ ባላት አስተዋጽኦ ሁላችንም ልናደነቃት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ሁሉም በሰው ልጆች አመጣጥ ታሪክ ላይ አቻ የማይገኝለት ቅርስ መገኛ በሆነችው አገር ሊኮራ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
ሉሲ /ድንቅነሽ/ ከ 50 አመት በኋላ በድጋሚ የሰው ዘር መገኛን ለማወቅ ያለውን ፍላጎት ያቀጣጠለች እንደሆነም ተናግረዋል።
ሉሲ የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት መለኪያና ማጣቀሻ መሆኗን ጠቅሰው በሰው ዘር ጥናት ላይ አዲስ በር የከፈተች መሆኑን ጠቁመዋል።
የሉሲ ግኝት በአፍሪካ ውስጥ ሥር የሰደዱ የዘር ግንዶች አንድ የጋራ መነሻ እንዳላቸው በጽኑ የሚመሰክሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ፓሌዮአንትሮፖሎጂ እና ፓሌዮንቶሎጂ ማህበር ፕሬዝደንት ዶክተር ጃክሰን ኔያው በበኩላቸው የሉሲ ግኝት የሰው ልጆችን ታሪካዊ አመጣጥ ለመገንዘብ ተነሳሽነት መፍጠሩን ገልጸዋል።
ስለ ሰው ልጆች አሁናዊና የወደፊት ዝግመተ ለውጥ ቅርሶች ጠቃሚ ግንዛቤን የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለቅርሶች ግኝት ዋጋ መስጠት እንደሚያስፈልግ እና በቀጣናው ስላለው የአርኪዎሎጂ ቅሪተ አካል ሃብትም ህብረተሰቡን ማስገንዘብ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን መሰል ስኬታማ ሁነት በማዘጋጀቱም ምስጋና አቅርበዋል።