ቀጥታ፡

ከለውጡ ወዲህ በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ተግባራት የጤናን ፍትሃዊ ተደራሽነት እያሳደገ ነው -- ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ

ድሬደዋ፤ ሐምሌ 22/2016 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ተግባራት የጤናን ፍትሃዊ ተደራሽነት እያሳደገ መምጣቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ይህን የገለጹት ከ420 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በድሬዳዋ የተገነባው ሀሴት ሜድቴክ የህክምና ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካን ከሌሎች የፌዴራልና የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።


 

ወይዘሮ ፍሬህይወት እንዳሉት የጤና ግብዓትን በሀገር ውስጥ ለማምረት በተደረገው ርብርብ 36 በመቶው ግብዓት በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል።

በቀጣይም የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያመላከተ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው፤ዛሬ ተመርቆ ስራ የጀመረው የጤና ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ ዘርፉን ከማሻሻል ባለፈ የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ተግባራት የጤናን ፍትሃዊ እና ተደራሽነት እያሳደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካም የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም ባለድርሻ  አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ ናቸው።

ይህንን ዕውን ለማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሠረታዊ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት በዘርፉ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸዋል።

እነዚህን ስራዎች ይበልጥ በማሳደግ በኩል በውጭ አገራት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን እያበረከቱ የሚገኙትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በተደረገ የተቀናጀ ድጋፍም ዛሬ ተመርቆ ማምረት የጀመረው ፋብሪካ እውን መሆኑን  ተናግረዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገ የተቀናጀ ድጋፍ በአስተዳደሩ ሁለንተናዊ ለውጦችና ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በተለይም ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱና የውጭ ምንዛሬ እያሰገኙ ያሉ ፋብሪካዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ለአብነት በማንሳት።

ዛሬ ተመርቆ  ምርት የጀመረው የጤና ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካ የውጭ ምንዛሬን በማዳንና በማስገኘት እንዲሁም የስራ ዕድል በመፍጠር አበርክቶው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሃብት የተገነባው ፋብሪካው ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ሃብት፣ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ በስራ ላይ በማዋል ለአገር እድገት እያበረከቱ የሚገኙ አስተዋፅኦ እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀጣይም አስተዳደሩ በውጭ አገራት የሚገኙት የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በተለያዩ ልማቶች ላይ እንዲሳተፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አረጋግጠዋል።

የፋብሪካው ባለቤት አቶ ሲሳይ በቀለ፣ የድሬዳዋ አስተዳደርና የፌደራል ተቋማት በቅንጅትና በተናጠል የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት  ሃብቱን፣ ዕውቀቱንና ያካበተውን ልምድ በስራ ላይ እንዲያውል የሚያደርጉት ደጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር በቀን ከ500 ሺህ በላይ ሲሪንጅ ከነመርፌው ማምረት ይችላል ብለዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የፌደራል እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የአመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም