ሀሴት ሜዲቴክ የህክምና መገልገያ ቁሶች ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ማምረት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሀሴት ሜዲቴክ የህክምና መገልገያ ቁሶች ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ማምረት ጀመረ
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር በ420 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሀሴት ሜዲቴክ የህክምና መገልገያ ቁሶች ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቆ ማምረት ጀመረ።
ፋብሪካውን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሐመድን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት ናቸው።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሠረታዊ ድጋፍ የተደረገለት ይህ የተለያዩ የህክምና ግብዓት እና የህክምና ቁሳቁስ የሚያመርተው ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል።
ፋብሪካው የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት እንቅስቃሴዎች ካስገኛቸው ውጤቶች አንዱና የትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን የልማት ተሳትፎ ማሳያ መሆኑም በምረቃው ስነ ስርአት ላይ ተመልክቷል።
የአሜሪካ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በ420 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ወደ ማምረት የተሸጋገረው ይህ ፋብሪካ፤ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን የሚያስቀር መሆኑን በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ እና የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ፋብሪካውን የፌዴራል የሥራ ሃላፊዎችና የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር መርቀው ከፍተዋል ።