የፍራፍሬ ችግኞች ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፍራፍሬ ችግኞች ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ እያስገኙ ነው
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከሏቸው የፍራፍሬ ችግኞች ገቢ በመፍጠር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጡ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
አርሶ አደሮቹ ዘንድሮ በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞች እየተከሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተከሏቸው ችግኞች ጎርፍ በማሳቸው ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ከመከላከል በተጨማሪ ለግብርና ስራቸው ተስማሚ የአየር ንብረት መፍጠር ችሏል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል የሐርላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱላሂ ጃማ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እና የተፋሰስ ልማት ሥራው የጠፉ ምንጮች እንዲጎለብቱ በማስቻሉ በአነስተኛ መሬት ላይ የተከሏቸው የተለያዩ ፍራፍሬ ችግኞች ማፍራት ጀምረዋል።
በተለይም ቀደም ሲል የተተከሉት የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች ማፍራታቸው አርሶ አደሩ ከቤተሰቡ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት አስችለዋል ብለዋል።
የተገኙትን ውጤቶች ለማስቀጠልም በዘንድሮው ዘመቻ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን እየተከሉ መሆናቸውን በመጥቀስ።
ሌላው የቀበሌው ነዋሪ ወጣት ሃምዛ አብዱላሂ በበኩሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቱሪዝም መዳረሻና የጥንታዊ መካነ መቃብር ሙዚየም ያለበት ቀበሌያቸውን ለቱሪስቶች ሳቢ ስፍራ እንዲሆን እያገዘ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣቶች በዘመቻው በሙሉ አቅማችን ተሳትፈን ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆንና ቀበሌውን ለቱሪስቶች ውብና ተስማሚ ስፍራ ለማድረግ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ብሏል።
የገንደ ሪጌ ቀበሌ አርሶ አደር አብዲ አህመድ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተከሉት በአጭር ጊዜ ለፍሬ ከሚደርሱት የፍራፍሬ ችግኞች ገቢ በማግኘት የቤተሰብ የምግብ ዋስትናቸውን የማረጋገጥ ሂደትን እያሳኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ወራት ለገበያ ካቀረብኳቸው የፓፓያ እና የሎሚ ምርቶች ብቻ 25 ሺህ ብር ገቢ አግኝቻለሁ፤ ይሄ ደግሞ ልጆቼን በአግባቡ ለማስተማር አግዞኛል በማለት ለአብነት ያነሳል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት አምስት ዓመታት ውሃ ገብ በሆኑ ቀበሌዎች የመስኖ ተጠቃሚ ማድረጉ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻውን ፍሬያማ እንዲሆን ማስቻሉን የገለፁት ደግሞ የለገ ኦዶ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር አልዪ አህመድ ናቸው።
የተፋሰስ ልማቱ፣ የሌማት ትሩፋቱና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮቹ የገጠሩን ማህበረሰብ ህይወት እንዲለወጥ እና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያገዙ በመሆኑ "በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትናችንን እናረጋግጣለን" ብለዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ወጣቶች በብዛት ተደራጅተው በማሳቻው ውስጥ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በመትከል ላይ መሆናቸውን የገለፀው ደግሞ የኮሪሶ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ዩሱፍ ሁሴን ናቸው።
አካባቢያችን ለዘመናት የፍራፍሬ አብቃይ ነው፤ ጥቅሙንም እናውቀዋለን፤ በስፋት እየተከልን የምንገኘውም ለዚሁ ነው ብለዋል።
የአዳዳ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ዘይቱና ሁሴን በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እና የተፋሰስ ልማት ከተጀመረ ወዲህ የጠፉ ምንጮች እና ቁጥቋጦዎች እየተመለሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አሁን በቀላሉ ውሃ እናገኛለን፤ ጊዜያችንና ጉልበታችንን ለእርሻ ስራችን እያዋልን ነው፤ የተከልናቸው ፍራፍሬዎች ዘንድሮ ማምረት ጀምረዋል ብለዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ፍራፍሬ ችግኞች በጋራ እና በቤት ለቤት እየተተከሉ መሆናቸውን ከድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።