የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተመራጮች እና ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ በክልሉ ከሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም ከጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ከ1 ሺህ 300 በላይ የህብረተሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም፣ ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።
ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚወከሉ የህብረተሰብ ተወካዮችን ከየክልሎቹ ልየታ ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ የሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቋም ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት አበክሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት መጀመሩን ገልጸው በጋምቤላ ክልልም ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሰባት ቀናት የሚቆይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መጀመሩን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው የምክክር ሂደት የሁሉም ድምጽ የሚሰማበትንና የመፍትሔ አማራጮች የሚቀመጡበትን ያስቀደመ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ዘላቂ ሠላምን በማረጋገጥ ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማት ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወያይተው፣ የአጀንዳ ሃሳባቸውን እንደሚያዘጋጁ እና እንደሚያቀርቡም ተመላክቷል።