የስልጤ ልማት ማህበር የጀመረውን የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራ በማጠናከር የአረንጓዴ ልማቱን ማገዝ አለበት--አቶ ኡስማን ሱሩር - ኢዜአ አማርኛ
የስልጤ ልማት ማህበር የጀመረውን የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራ በማጠናከር የአረንጓዴ ልማቱን ማገዝ አለበት--አቶ ኡስማን ሱሩር
ሐዋሳ ፤ ሐምሌ 21/2016(ኢዜአ)፦የስልጤ ልማት ማህበር የጀመረውን የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራ በማጠናከር የአረንጓዴ ልማት ሥራውን ማገዝ እንዳለበት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገለጹ።
የስልጤ ልማት ማህበር "ጉዞ ስልማ ለአረንጓዴ አሻራ" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አስተዳደር ቡርቃ ቀበሌ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በዚህ ጊዜ እንደገለጹት የስልጤ ልማት ማህበር ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ስራዎችን አከናውኗል።
ከእነዚህ መካከል አካባቢን የማልማትና የመጠበቅ ሥራ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ማህበሩ በአካባቢ ጥበቃ ልማት የጀመረውን ሥራ በማጠናከር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ አሻራውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በልማት ማህበሩ በተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በተለያዩ ወረዳዎች አረንጓዴ ፓርኮች መበራከታቸውን የጠቀሱት አቶ ኡስማን፣ "ልማት ማህበሩ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል።
የሚተከሉ ችግኞች ለቀጣይ ትውልድ ተሸጋግረው ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አቶ ኡስማን አክለውም በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የአፈር ለምነት በማሳደግ የግብርና ምርታማነት መጨመራቸውን ገልጸው፣ የልማት ማህበሩ ስራም ይህን በማገዝ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው ልማት ማህበሩን በአዲስ መልክ ለማጠናከር የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
ፍኖተ ካርታው ማህበሩ የህዝብ ተጠቃሚነትን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በሚያስችለው ልማቶች ላይ እንዲያተኩር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በእዚህም ማህበሩ በአረንጓዴ ልማት ነባር የችግኝ ጣቢያዎችን የማጠናከርና አዳዲስ ጣቢያዎችን ካማቋቋም ባለፈ ችግኝ የመትከልና እንክብካቤ የማድረግ ሥራዎችን ግብ አድርጎ ይሰራል ብለዋል።
ልማት ማህበሩ በፍኖተ ካርታው ያስቀመጣቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት በግንባር ቀደምነትነት እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል ናቸው፡፡
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከተማ አስተዳደሩ ለልማት ማህበሩ ሥራ ስኬት የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሀግብሩ የተሳተፉት አቶ አሊ አብደላ በበኩላቸው በችግኝ ተካላ መርሃ ግብር በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢው ህዝብ በልማት ሥራዎች የመሳተፍ ልምዱ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአካባቢን ገጽታን በሚቀይረው የችግኝ ተካላ በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራን ማሳረፍ ለትውልድ ምቹ አካባቢን ማውረስ ስለሆነ በጎ ሥራዎችን ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ሥራ ሃላፊዎች፣ የልማት ማህበሩ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።