ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከህብረተሰቡ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2016(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከህብረተሰቡ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም፤ በ2016 በጀት ዓመት ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ያደረገውን ድጋፍ፣ ትብብርና እገዛ በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሀገር ቤት እና በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ለግድቡ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ እገዛ በማስቀጠል ረገድ በጽህፈት ቤቱ በኩል የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከ8100 A አጭር የፅሁፍ መልእክት፣ ከፒን ሽያጭና ከሌሎች መንገዶች ገቢ ማሰባሰብ ማቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 1 ቢሊዮን 712 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በባለፈው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውሰው የዘንድሮው የተሻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረትና ርብርብ የዜጎች ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ የአካባቢውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወነ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም