ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት አጸደቀ

አሶሳ፤ ሐምሌ 21/2016(ኢዜአ)፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ስራ ማስኬጃ የሚሆን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት አጸደቀ።

የክልሉ ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬ ውሎው የክልሉን የዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት ሪፖርት ከማድመጡ በተጨማሪ የክልሉን የ2017 ዓ.ም በጀት አጽድቋል።

በዚህም ለክልሉ ለ2017 በጀት ዓመት በጀት 8 ቢሊየን 974 ሚሊየን 531 ሺህ 586 ብር ሆኖ ጸድቋል።


 

የበጀት ዕቅዱን ያቀረቡት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ እንደገለፁት 4 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ከክልሉ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን 3 ቢሊዮን 784 ሚሊየን 430ሺህ ብር ደግሞ ከፌዴራል መንግስት የሚገኝ ድጎማ ነው።

ቀሪው ከዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ፣ ከውጪ እርዳታ እና ከተቋማት ገቢ እንደሚሰበሰብም ተናግረዋል።

በጀቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የስድስት በመቶ ብልጫ እንዳለውም አቶ ዚያድ ተናግረዋል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት አስፈጻሚ አካላት በጀቱን ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ የምክር ቤቱ አባላት ክትትሉንና ቁጥጥሩን ሊያጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም ከኃላፊነት ለሚነሱ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅሞችን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም