የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በማህበራዊ ልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ ነው - ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በማህበራዊ ልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ ነው - ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 21/2016(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በማህበራዊ ልማትና በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሚሳተፉበት ሶስተኛው አመታዊ የድሬ ናፍቆት በዓል ከትናንት ምሽት ጀምሮ እየተካሄደ ነው።
በበዓሉ ላይ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እና በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እየተሳተፉ ነው።
ከንቲባ ከድር ጁሃር በስነ-ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ባለፉት ሁለት አመታት የተከበረው የድሬ ናፍቆት በዓል የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የእርስ በርስ ግንኙነትና ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ያጠናከሩበት ነው።
በተለይ በመላው ዓለም የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬዳዋ ማህበራዊ ልማቶች ላይ በመሳተፍ መሠረታዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።
እንዲሁም በተመቻቸላቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን በስራ ላይ በማዋል በማምረቻ፣ በጤና፣ በሆቴል፣ በንግድና ሌሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርተው በሺህ ለሚቆጠሩ ወገኖች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በበጎ ፈቃድ ስራዎች እና በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻዎች ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህን መሠረታዊ ውጤቶች ይበልጥ ለማሳደግ የድሬ ናፍቆት በዓል ጥሩ መደላድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በድሬዳዋ አሸዋ የገበያ ማዕከል እና በጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና በማቋቋም የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ትናንት ምሽት በተጀመረውና ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የድሬ ናፍቆት በዓል ላይ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አመራሮች ተሳትፈዋል።