ባለኃብቶች መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በገነባቸው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ባለኃብቶች መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በገነባቸው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦ ባለኃብቶች መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በገነባቸው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እያለሙ ከሚገኙና አዳዲስ ባለኃብቶች ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ምክክር አካሂዷል።
በመድረኩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ጨምሮ የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችና ባለኃብቶች ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአራቱም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግንባታ መሠረት የሚጥሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህም የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ገበያ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ችግር የሚፈታ መሆኑንና በሌላ በኩል ደግሞ ለአምራች ባለኃብቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
እስካሁን ድረስ በለሙት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ውጭ በሚልኳቸው ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ መሆኑን አመላክተዋል።
ፓርኮች ከመገንባት ባሻገር ለአምራቾች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን ምቹ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም እየገጠሙ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ አዳዲስ ባለኃብቶች ቢገቡ ውጤታማ እንደሚሆኑና ክልሉም ለፓርኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባለኃብቶች በአቮካዶ ዘይት፣ በማር፣ በወተትና በቡና ምርቶች ላይ ተሠማርተው እየሠሩ እንደሚገኙ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።