ቀጥታ፡

አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎች የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016 (ኢዜአ)፦አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎች ትክክለኛ መረጃ በመሰብሰብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጠየቀ። 

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ∙ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30/2017 ዓ∙ም ድረስ አምስተኛውን የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።

ጥናቱ የሚካሄድባቸውን ሥፍራዎች የመለየት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የሚሰበስቡ አካላትን የማዘጋጀትና ሌሎች ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል። 


 

በዛሬውም ዕለት አገልግሎቱ በአገሪቱ የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ላይ መረጃ ለሚያሰባስቡ ከ450 በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች ባለፉት ሁለት ወራት ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና አጠናቋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መርኃ ግብር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጥራቱን የጠበቀ የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት መረጃ በተገቢው ማጥናት  ፖሊሲዎችን ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል።

እንዲሁም ልዩ ልዩ እቅዶችን በማውጣት ተፈጻሚነታቸውን ለመከታተልና ቀጣይነት ያለው አገራዊ እድገት ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ተናግረዋል። 

ይህንንም ለማረጋገጥ የሚጠኑ ጥናቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ባሟላ መልኩ ማካሄድና ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የገለጹት። 

በዚህም በቀጣይ በሚካሄደው አምስተኛ ዙር የሥነ- ህዝብና ጤና ጥናት ውጤታማ እንዲሆን የመረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው አምስተኛው ዙር የሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ለማድረግ በሰው ኃይል በግብዓትም በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።


 

በዛሬውም ዕለት በመላ አገሪቱ ተሰማርተው መረጃ ለሚሰበስቡ ባለሙያዎች አገልግሎቱ ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ለመግባት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ጥናቱ ውጤታማ እንዲሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።  

በመረጃ አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ተአማኒኒነት ያለው መረጃ ለማሰባሰብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም