ቀጥታ፡

ባለፈው በጀት ዓመት ህገ-ወጥ ንግድንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ውጤት ተመዝግቧል-ኮሚሽኑ

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 20/2016 (ኢዜአ)፡-በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ-ወጥ ንግድንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ውጤት መመዝገቡን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በ2016 የበጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2017 ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ እየመከረ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ-ወጥ ንግድንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ውጤት ተመዝግቧል።

በአገሪቱ በገቢና ወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን ህገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው የተቀናጀ እንቅስቃሴ ስኬታማ  ነበር ብለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 119 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት በገቢና በወጪ እንዲሁም ህጋዊ ሰነድ ባላቸው ዕቃዎች ሽፋን ሲንቀሳቀስ መያዙን አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥ 17 ቢሊዮን ብር የሚሸፍነው የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ የወጪ ዕቃዎች እንደሆኑ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ ህገ-ወጥ ንግድንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ብሎም ሀገሪቱ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ይሰራል ብለዋል።

ለዚህም ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከተለያዩ አካላት ጋር ጠንካራ የህግና የኦፕሬሽን ማዕቀፎችን በመዘርጋት እንደሚሠራም ኮሚሽነር ደበሌ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ ላይ የሚያደርገውን ውይይት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚያካሄድም ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም