ቀጥታ፡

ብክለትን ለመቀነስ የተጀመረውን ንቅናቄ በማጠናከር በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው

አዳማ፤ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦ብክለትን ለመቀነስ የተጀመረውን ንቅናቄ በማጠናከር በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ የአካባቢ ብክለትን ለመግታት ''ብክለት ይብቃ፣ ውበት ይንቃ'' በሚል መሪ ሃሳብ ሲያካሄድ በቆየው የህዝብ ንቅናቄ ላይ ያተኮረ ውይይትና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ በአዳማ አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ባለፉት አራት ወራት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎች ተሰርተዋል።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ በፌዴራልና በክልሎች ሲከናወን የቆየው የብክለትን የመከላከል ንቅናቄ በትኩረትና በቅንጅት ከተሰራ የሚፈለገውን ለውጥ በአጭር ጊዜ ማምጣት እንደሚቻል አመላካች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተለይም በፕላስቲክ አወጋገድ ላይ የተሰራው የተቀናጀ ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው ይህም በአፈር ጥበቃ ላይ የሚሰራውን ሥራ ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ንቅናቄውን በመገምገም መስተካከል በሚገባው ጉዳይ ላይ ማተኮርና በቀጣይ ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስገንዝበዋል፡፡

''በአካባቢ ጥበቃ ላይ ዛሬ የተሰራው የነገ መሰረት ነውና ሁሉም በቅንጅት በመስራት እንደ ሀገር የተጣለብንን ኃላፊነት በጋራ እንወጣ'' ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈዲን መኸዲ፣ ባለፉት ወራት በተከናወነ ብክለትን የመከላከል ንቅናቄ በክልሉ ውጤት ማምጣት መጀመሩን አንስተዋል።

ወጣቶች በስፋት ተደራጅተው አካባቢን ከፕላስቲክ ብክለት ነፃ ከማድረጋቸው ባሻገር፤ ቆሻሻን ወደ ሀብት እንደቀይሩም  ተናግረዋል፡፡

በንቅናቄው በርካታ ሕዝብ በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጥ መደረጉን ገልጸው ''ንቅናቄው ቆሻሻን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን አወጋገዱን ማዘመን የራሴ ጉዳይ ነው የሚል ማህበረሰብ እስኪፈጠር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት'' ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የሲዳማ ክልል የአካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ተወካይ አቶ ዮሴፍ ክቡ፣ ንቅናቄውን በክልሉ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የውሃ ሀብቱን ከፕላስቲክ ብክለት ለመታደግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ከህብረተሰቡ ጋርም በተደረገ ውይይትም ቆሻሻን ወደ ሀብትና የስራ እድል በመቀየር ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን  አስታውቀዋል፡፡ 

በቀጣይም የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱ አካባቢን ለመፍጠር ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል ተወካዩ፡፡

በመድረኩ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮችና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም