ቀጥታ፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ዜጎችን ሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ። 

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆኑት አህመድ ማንሶሬ (ዶ/ር) ድጋፉ በደረሰው የመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ዜጎች የሚውል ነው።

ድጋፉ የሁለቱ አገራት ወዳጅነትን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዛሬ ለኢትዮጵያ ያደረገው የ85 ቶን የሰብዓዊ ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚኖር ተናግረዋል።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ድጋፉ በአደጋው ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በፈተናም በደስታም ጊዜ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን አጋር ሆኖ መቆሙን ጠቅሰው ዛሬ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት እስካሁን የ231 ዜጎች ሕይወት ማለፉንና ከሟቾቹ የ18 ሰዎች አስከሬን አለመገኘቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ገልጿል። 

በአደጋው ምክንያት ከ500 በላይ ወገኖች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፤ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ከአደጋ ሥጋት ቀጣናው እንዲወጡ በጥናት ላይ የተመሠረተ እርምጃ ለመውሰድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሷል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ወረዳ የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ሕይወታቸው ላለፉ ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን በትላንትናው ዕለት አውጇል።

በእነዚህም ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም