በመከላከያ ስር በሚገኙ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ኢ/ር አይሻ መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
በመከላከያ ስር በሚገኙ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ኢ/ር አይሻ መሀመድ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦ በመከላከያ ስር በሚገኙ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሀመድ ገለፁ።
የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሀመድ በመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን የሪፎርምና የልማት ስራዎች ጎብኝተዋል።
በዚህም የመከላከያ ግንባታ ግብዓት ማምረቻ ድርጅት፣ በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ እየተገነባ ያለውን የባህር ሀይል ዋና መስሪያ ቤት፣ የአዳማ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪና የአየር ወለድና ኮማንዶ ዋና መስሪያ ቤት የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የጉብኝቱ ዓላማ በተቋማቱ ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ያለመ ነው።
በተቋማቱ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርምና የልማት ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት ሪፎርም በማድረግ የሰው ሃይልና የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማሟላት የእንጨትና የብረታ ብረት ውጤቶችን በስፋት በማምረት አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ በራሱ አቅም እየተገነባ ያለው የባህር ሃይል ዋና መስሪያ ቤት ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ የሚጠናቀቅበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንዲሁም የኮማንዶና አየር ወለድ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ በታቀደው ጊዜና ጥራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዳማ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪም ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር ለሰራዊቱ የሚያስፈልጉ አልባሳትና ቁሳቁስን ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሰራዊቱን አልባሳትና ዘመናዊ ትጥቆች በስፋት በማምረት በዘንድሮው እቅዱ 50 በመቶ የሰራዊቱን አልባሳት መሸፈን መቻሉን ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪው የሰራዊቱን አልባሳት ከማሟላት ባለፈ ለሌሎች የፀጥታ አካላትና ለተለያዩ ተቋማት የደንብ ልብስ በማምረት ለውጭ አገራት ለመላክ የሚያስችል አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
በቀጣይ ኢንዱስትሪው ከአገር ውስጥ አልፎ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግለታል ብለዋል።
ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተደረገው ጉብኝት ለክፍሎቹ ተደማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።