በበጀት ዓመቱ ከ190 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል-ጉምሩክ ኮሚሽን

አርባምንጭ ፤ ሐምሌ 20/2016 (ኢዜአ)፡- የጉምሩክ ኮሚሽን በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ከ190 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።

የጉምሩክ ኮሚሽን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዕቅድ ላይ የሚመክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው ።


 

በመድረኩ ላይ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ባደረጉት ንግግር ፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ190 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የተቋሙን ዕቅድ 91 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤  ገቢው የተሰበሰበው ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ እና ከሌሎች ታክስ እና ታክስ ካልሆኑ አርዕስቶች  ነው።

ኮሚሽኑ የሀገሪቱን  ኢኮኖሚ የሚመግብ የገቢ ንግድ ሥርዓት በማበጀት ሀገሪቱ ከዘርፉ ተገቢውን ገቢ እንድታገኝ የተቀናጀ ተግባር መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የሀገሪቱ ብልጽግና እውን እንዲሆን አበክሮ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ብሎም የንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ ለመከላከል በተደረጉ ጥረቶች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል ኮሚሽነር ደበሌ።

በዚህም ከኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የህግ ማስከበር ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ በመሰራቱ በርካታ ሀብት ማዳን መቻሉንም ጠቅሰዋል  ።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የምክክር  መድረኩ የገቢዎች ሚኒስቴርን ጨምሮ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ  ወገኖች የህሊና ፀሎት ያደረጉ ሲሆን፤ ለተጎጂ  ቤተሰቦች  ድጋፍ እንደሚደረግም ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም