ቀጥታ፡

በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው- አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ) በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በማስተዋወቅ ዘርፉን ለማዘመን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ  አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ግሎባል ትሬድ ኤንድ ፋይናንስ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችለው የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።


 

ስምምነቱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ የግሎባል ትሬድ ኤንድ ፋይናንስ  ፕሬዝዳንት  ኬ ጄ ሊ ፈርመዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን እምቅ ፍላጎትና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በማስተዋወቅ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ዘርፉ ገና ያልተሰራበትና ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ያለበት በመሆኑም በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት ውጤታማ እንደሚሆኑም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠምና የማምረት፣ በሎጂስቲክስ፣ በባቡር፣ በመንገድ መሠረተ-ልማትና የወደብ ግንባታ ሰፊ ዕድል መኖራቸውንም በዚሁ ወቅት ገልፀዋል።

የዛሬው ስምምነት ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለሃብቶች በዘርፉ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው እንዲሰማሩ ለማድረግ ነው ብለዋል።

የግሎባል ትሬዲንግ  ኤንድ ፋይናንስ ፕሬዝዳንት ኬ ጄ ሊ በበኩላቸው፤በኢትዮጵያ ባለው ምቹ ኢንቨስትመንትና እድገት መሳባቸውንና ባለሃብቶችንም ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መወሰናቸውን ገልፀዋል።


 

በርካታ የአፍሪካ አገራትን ተዘዋውሮ ለመመልከት ዕድሉን ያገኘን ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች አገር መሆኗን በተጨባጭ ለማየት ችለናል ነው ያሉት።

በመሆኑም በተለያዩ አገራት ያሉ ባለሃብቶችን በመሳብ በኢትዮጵያ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ እንደሚሰሩም  ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም