ቀጥታ፡

አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል - ወይዘሮ ጥሩማር አባተ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና  ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎች ትክክለኛ የሆነ መረጃን ለመሰብሰብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ  ወይዘሮ ጥሩማር አባተ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በሀገሪቱ የሥነ- ህዝብና ጤና ጥናት ላይ መረጃ ለሚያሰባስቡ ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ በዚህ ወቅት እንደገለፁት  ጥናቱ ጤናና ማህበራዊ  የሆኑ መረጃዎችን ለማደራጀት ያግዛል ብለዋል፡፡

አምስተኛው ዙር የሥነ- ህዝብና ጤና ጥናት ውጤታማ እንዲሆን የመረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው ጥናቱ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ተቋማቶች ምስጋና አቅርበዋል።

አምስተኛው ዙር የስነ ህዝብና ጤና ጥናት ለማድረግ በሰው ሀይል በግብዓትም በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በዛሬውም ዕለት በመላ ሀገሪቱ ተሰማርተው መረጃ ለሚሰበስቡ ባለሙያዎች አገልግሎቱ ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ለመግባት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ከሀምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ መገለፁ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም