መንግስት በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚያደርሰውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚያደርሰውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚያደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት መንሸራተት ሳቢያ የደረሰውን ጉዳትና የመንግስትን ምላሽ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ- ኃይል በአካባቢው ተሰማርቶ ጉዳቱን ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳሚዋት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጋር በመሆን የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰበት ስፍራ በመገኘት ተጎጂዎችን አፅናንተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ የሀዘን ቀን አውጇል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊ ካሳ እንዳሉት፣ በአደጋው እስከ አሁን የ231 ዜጎች ሕይወት ማለፉንና ከሟቾቹ የ18 ሰዎች አስክሬን አለመገኘቱን ገልጸዋል።
በአደጋው ምክንያት ከ500 በላይ ወገኖች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች ከአደጋ ስጋት ቀጣናው እንዲወጡ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ ለመውሰድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ማወጁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ባለባቸው ሁሉ ዝቅ ብሎ መውለብለቡንም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
መንግሥት ለችግሩ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ለተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና እስካሁን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደራሽ መሆኑን አመልክተዋል።
የተለያዩ የዓለም ሀገራት በአደጋው ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆኑንም ገልጸው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 75 ቶን ምግብ ነክ ድጋፍ መላኳን አንስተዋል።