ቀጥታ፡

13ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦13ኛው አገር አቀፍ የመንግሥት  ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጉባዔ "ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ዕድል " በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎችና የዘርፉ ተዋናዮች ተገኝተዋል። 


 

'' ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ዕድል " በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ በጀመረው ጉባዔ በቴክኖሎጂ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ጽሑፎች ቀርበው ምክክር ይደረጋል ተብሏል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ እንደተናገሩት፤ ቴክኖሎጂ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ  እያከናወኑ ላለው ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ከተካተቱት ዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ  ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አንዱ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል።

በመሆኑም በትምህርት ዘርፉ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ የተቀመጡ ዓለም አቀፍ ግቦችን ለማሳካትና እየተደረጉ ያሉ ሪፎርምችን ለማሳካት ከፍተኛ ሚና እንዳለው  ጠቁመዋል።

አራተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት አዳዲስ እውቀት ያላቸው ተወዳዳሪ ሙያተኞችን ማፍራት የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በአጠቃላይና በከፍተኛ የትምህርት ሥርዓት በማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የተለያዩ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የመማር ማስተማሩን ሂደት የማዘመንና ዲጂታላይዜሽንን እውን የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጨምረው ተናግረዋል።

በጉባዔውም ለከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ ግብዓትና በዘርፉ ተጨማሪ ምርምሮች ለማካሄድ  የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተሻለ ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም