ዶክተር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ስምምነት ልዑክ ቡድን መሪ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ዶክተር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ስምምነት ልዑክ ቡድን መሪ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ስምምነት ልዑክ ቡድን መሪ ሮቤርቶ ስኪሊሮ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም የኢትዮጵያ ቡና በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ገበያ በስፋት እንዲቀርብ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ ተመላክቷል።
የቡና ምርትን እሴት ሰንሰለት ለማሳደግና የውጭ ገበያ አማራጮችን ለማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።
በኢኮኖሚና ሌሎች ጉዳዮች በትብብር እየሰሩ የሚገኙት ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በትብብር እየሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቡና በህብረቱ አባል ሀገራት ገበያ በስፋት ለማቅረብ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በጋራ እየሰሩ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የቡና የአቅርቦቱና እሴት ሰንሰለቱ ከአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ነጻ ደንብ ጋር መጣጣም እንዳለበትም ተገልጿል።