ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት የቅድመ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በምሳሌነት የተነሳበት ነው - አቶ   አሕመድ ሽዴ

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት የቅድመ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በምሳሌነት የተነሳበት ነው - አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በ4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት የቅድመ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የለውጥ እርምጃ በምሳሌነት የተነሳበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከሐምሌ 15 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የቆየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ተጠናቋል።

ጉባኤውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፤ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በመዲናዋ "የአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳ" ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ማስተናገዷን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም የዘንድሮውን 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የተደረሱ ውሳኔዎችን በመገምገም በስፔን ለሚካሄደው ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ስራዋን በስኬት አስተናግዳለች ብለዋል።


 

በጉባኤው ላይ የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት፣ የድርጅቱና የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተሳተፉበት በስኬት ተካሂዶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በዚህም ቅድመ ጉባኤው በስፔን ለሚካሄደው የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የታዳጊ ሀገራትን ዕድገት ታሳቢ በማድረግ የለውጥ እርምጃ መወሰድ እንዳለባቸው ተመላክቷል።

የውሳኔዎቹ አተገባበርና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የታዳጊ ሀገራት ውክልና እና ለልማት የሚቀርበው የገንዘብ ድጋፍ ማደግ እንዳለበት ዋና ዋና የቅድመ ጉባኤው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ታዳጊ ሀገራትም ምቹ የልማት ምህዳር በመፍጠር የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማሳደግ የገቢ አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው በቅድመ ጉባኤው ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የአፍሪካንና ታዳጊ ሀገራትን ድምጽ በማሰማት ሂደትም ኮንፍረንሱ ስኬታማ ነበር ብለዋል።

አዲስ አበባም በስኬታማ የኮሪደር ልማት የቱሪዝም መዳረሻ ስራዎቿ ተውባና ደምቃ እንግዶቿን በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ እንደቻለች አስረድተዋል።

የቅድመ ጉባኤው ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን የመዲናዋን የአፍሪካ ማዕከልነት ታሳቢ በማድረግ የተከናወኑ መሆናቸውን በአድናቆት እንደገለጹ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የወሰደችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጠናክራ በመቀጠል የተሻለ ለውጥ የምታመጣ ሀገር መሆኗን በምሳሌነት የተነሳበት እንደነበር አስታውቀዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ልዑልሰገድ ታደሠ፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ሥርዓት የታዳጊ ሀገራትን የልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያ ማድረግ እንዳባቸው ታምናለች ብለዋል።


 

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍም ዘላቂ ልማት ግቦችን መፈጸም በሚያስችል መልኩ አሳታፊና ሁሉን ዓቀፍ መሆን እንዳለበት ድምጿን ስታሰማ እንደቆየች ገልጸዋል፡፡

"በአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳ" ፍትሕዊ የዓለም አቀፍ ገንዘብ ሥርዓት እንዲፈጠር መወሰኑን አስታወሰው፤ በኮንፍረንሱም ፍትሕዊ የገንዘብ ተቋማት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው በአጀንዳነት ተይዟል ብለዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፤ በስኬት ለተጠናቀቀው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ስኬት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ የተቋማት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቅድመ ጉባኤው ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ በመንቀሳቀስ በመዲናዋ የተመዘገበውን ተጨባጭ የኮሪደር ልማት ለውጦች በአድናቆት ምላሽ መስጠታቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ትክክለኛ መገለጫ ልማትና ብልጽግና ነው ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ የቅድመ ጉባኤው ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ተገንዘብው እንደሚሄዱ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

በጉባኤው ላይ የመንግስታቱ ድርጅት የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ሊ ጁንዋ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክላቨር ጋቴቴ ጨምሮ ከ850 በላይ የድርጅቱ አባል ሀገራት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።

የተጠናቀቀው 4ኛው የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ልማት የቅድመ ጉባኤ እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3/2025 በስፔን ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የተዘጋጀ መድረክ አካል መሆኑ ተገልጿል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም