ቀጥታ፡

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በበጀት አመቱ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት ፈፅሟል- ጀነራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦
የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በበጀት አመቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት መፈፀሙን የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ አረጋገጡ።

ጀነራል መኮንኑ ይህንን ያረጋገጡት ዕዙ ከክፍለ ጦር አመራሮች እና ከመምሪያ ኃላፊዎች ጋር ለሁለት ቀናት ባደረገው ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ነዉ።

ጀነራል አበባው ታደሰ አሁን ባለው እውነታ ፅንፈኛው ኃይል ተመቷል፤ የቀረውም ቢሆን በሰፈር እና በጎጥ ተከፋፍሎ በስልጣን ፍላጎትና በሰበሰበው ገንዘብ እየተጣላ እንዲሁም እርስ በርሱ እየተገዳደለ እና አንዱ በአንዱ ላይ እየዘመተ ተራ ሽፍታ ሆኗል ነው ያሉት።

በውሸት ፕሮፓጋንዳ የአማራ ህዝብ ጥያቄ ከሌላኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የተለየ አስመስሎ ሲሰብከው የነበረው ማህበረሰብም የፅንፈኛውን ሴራ አውቆበት ይህን ቡድን መደገፍም ሆነ መርዳት እንደማያስፈልግ መግባባት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።


 

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ከአሁን በፊት በነበሩት በርካታ ግዳጆችም ወደር የሌላቸው አኩሪ ገድሎችን የፈፀመ ጀግና ክፍል መሆኑን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ሰዓት አቅሙን አጎልብቶ በበቂ ደረጃ የተደራጀ በመሆኑ በቀጣይም ብዙ የሚጠበቅበት የማይበገር የህዝብና የሃገር ትልቅ አለኝታ ስለሆነ የቀጣይ ተልዕኮውንም በውጤት ይፈፅማል ብለዋል ጀነራል አበባው ታደሰ።

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ በበኩላቸዉ የክፍሉ የሠራዊት አባላት ከላይ እስከታች እጅና ጓንት ሆነው ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት በጋራ በመሥራታቸው በአመቱ ክፍሉ የሚፈለገውን ድል ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

 

ሃገሩን እና ህዝቡን እያሰበ የሚሰራ ሠራዊት እና ለሃገር እና ለህዝብ የቆመ ሃይል ሁሌም አሸናፊ ነው ብለዋል የእዙ አዛዥ።

ከዚህ የተነሳም በሰንደቅ አላማዋ ስር በገባነው ቃል መሠረት ለህዝባችን ለሃገራችን በትጋት በፍፁም ጀግንነት በመስራት ሰላሙን በዘላቂነት በማረጋገጥ ሀገራዊ ልማትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ያለ እንቅፋት እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅብናል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም