ቀጥታ፡

በክልሉ በከተማ ልማት ክላስተር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት ተመዝግቧል-አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር )

ደሴ ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በከተማ ልማት ክላስተር የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማከናወን አበረታች ውጤት መመዝገቡን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር ) ገለጹ። 

የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ክላስተር የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሄዷል።


 

አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የከተማ ልማት ክላስተሩን በመደገፍና በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ኢኮኖሚውን ያነቃቃ ተግባር ተከናውኗል።

በዚህም  በስራ እድል ፈጠራ፣ ከተሞችን በሁለንተናዊ መንገድ በማልማት፣ ገበያውን በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን በመከላከል፣በኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማ ልማት ክላስተር የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማከናወን አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ/ር)በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል።

በዚህም መንግስት በመደበው 689 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር እና ዩኒየኖችና ህብረት ስራ ማህበራት በራሳቸው በመደቡት 420 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ምርት ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም 713 ሺህ ኩንታል በላይ ኢንዱስትሪና የግብርና ምርት እና አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

 አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ መሳብ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ናቸው። 

በዚህም ከ564 ሺህ ቶን በላይ ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ምርት በአገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አብራርተዋል።

በተለይም ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ውጤት እንዲመዘገብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ከ44 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች  የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።

እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ437 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ  2 ሺህ 650 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል።

የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ፤ በክልሉ የመሬት አያያዝና አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተደረገው ጥረት አበረታች ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም ከ388 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም 3 ሺህ 200 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ከአበዳሪ ተቋማት ከ161 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲወስዱ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም