ቀጥታ፡

ትብብር የሰፈነበትን አዲስ የአለም አሰላለፍ ዕውን ለማድረግ የጋራ ድምጻችን ጉልህ ሚና ይጫወታል- የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ትብብር የሰፈነበትን አዲስ የአለም አሰላለፍ ዕውን ለማድረግ የጋራ ድምጻችን ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና ገለጹ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በተሳተፉበት የብሪክስ የወጣት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆና በመቀላቀሏ ኩራት አንደሚሰማት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሁሉም የብሪክስ አባል አገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ለአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ያላትን ቁርጠኝነት በጉልህ ያንጸባርቃል ሲሉም ተናግረዋል።

በአዲሱ የአለም አሰላለፍ ውስጥ ብሪክስ ፍትሀዊነትና አካታችነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ ጽኑ እምነት መሆኑንም አስረድተዋል።


 

ትብብር የሰፈነበትን አዲስ የአለም አሰላለፍ ዕውን ለማድረግ በተለያዩ የአለም መድረኮች የጋራ ድምጻችንን ማሰማት ይጠበቅብናል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

በወጣቶች ዘርፍ ለሚኖረው የትብብር ማዕቀፍ ትምህርት፤ኢኖቬሽንና ስራ ፈጠራ እንዲሁም የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ለብሪክስ መጠናከር አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም