በኢትዮጵያ የተካሄደው 4ኛው የፋይናንስ ለዘላቂ ልማት ጉባዔ የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተካሄደው 4ኛው የፋይናንስ ለዘላቂ ልማት ጉባዔ የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ):- በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 4ኛው አለምአቀፍ የፋይናንስ ለዘላቂ ልማት ጉባዔ የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ተጠናቀቀ።
እ.ኤ.አ. ከጁላይ 22-26 ቀን 2024 ሲካሄድ የቆየው ጉባኤ ሲጠናቀቅ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ባለፉት አምስት ቀናት የተካሄዱት ውይይቶች ጥልቅ ሀሳቦች የተነሱበት መሆኑን ጠቁመው፣ መንሸራሸር ያለባቸው ሀሳቦችም በጉባዔው ለውይይት መቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።
በኮንፈረንሱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት፣ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያሉ የስርዓት ችግሮችን ለመፍታት እና በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ አለምአቀፍ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለመዘርጋት ያስቻለ መድረክ መሆኑንም ተጠቅሷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ጁንዋ ሊ በመዝጊያው ላይ በሰጡት አስተያየት ጉባኤው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመፍጠር መምከሩን አመልክተዋል።
ምክትል ዋና ጸሃፊ ጁንዋ ሊ ለጉባኤው ስኬታማነት የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገው ደማቅ አቀባበል እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።