ቀጥታ፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ማስገንዘብ  የቻለችበት ነው- አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ  

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በማስገንዘብ  ገጽታዋን ይበልጥ የገነባችበት ነው ሲሉ  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ ተናገሩ።

አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ከ193 አገራት የተወጣጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ተሳትፈውበታል። 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድን ጨምሮ በርካታ ተሳታፊዎች ታድመዋል።   


 

ጉባኤው እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2025  በስፔን ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የተዘጋጀ የቅድመ ጉባኤ መድረክ ሲሆን ልማትን ለማሳለጥ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት መዘረጋትን ዓላማ ያደረገ ነው።     

የታክስ አሰባሰብ ስርአትን በማጎልበት ሀብት አሰባሰብን ማጠናከር ሌላው ዓላማ ሲሆን አገራት ሀብት አሰባሰብ ላይ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።          

ኢትዮጵያም በመድረኩ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረጉ የፋይናንስ ስርዓቶች ሊዘረጉ እንደሚገባ አቋሟን አንጸባርቃለች።         

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት ብለዋል።

 

የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ኢትዮጵያ ሁሌም ተሳታፊ ናት ያሉት አምባሳደሩ ጉባኤው ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት መሆኑን አብራርተዋል።  

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ፣የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ጨምሮ የልማት እንቅስቃሴዎቿን ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በሰፊው ማስገንዘብ የተቻለበት መሆኑን አስረድተዋል። 

እንደ አምባሳደር ሳሙኤል ገለጻ በጉባኤው በተካሄዱ የባለሙያዎች ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያ በየዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ማስረዳት ተችሏል።      

ጉባኤው ስኬታማና ግቡን ያሳካ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ገጽታ ይበልጥ ማስተዋወቅ የተቻለበት ነው ሲሉም ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ያለው ሠላምና መረጋጋት ትልልቅ ጉባኤዎችን እየሳበ መሆኑን ጠቅሰው አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።  

ከዚህ አኳያ ጉባኤው ኢትዮጵያ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን ያረጋገጠ ከመሆኑ በላይ የአገልግሎት ዘርፉን የማነቃቃት ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።

 

 

 

   

 

 

 

 

 

                    

 

     

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም