ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን  አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ በ2016 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የ2017 ዓ.ም እቅድን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻር ተቋሙ 51 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን በማስታወስ፤ አፈጻጸሙ ግን ከፍተኛ እመርታ በማሳየት 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም አክለዋል።

በተመሳሳይ በ2016 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 70 ቢሊየን ለማትረፍ አቅዶ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ  መገኘቱንም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የተገኘው የገቢም ሆነ የትርፍ ምጣኔ ከእቅዱ አንጻር መቶ በመቶ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑንም አክለዋል።

ይሁንና በዓለም ላይ ባሉ በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ መርከቦች በታለመላቸው ልክ እቃዎችን እንዳያጓጉዙ እንቅፋት መሆኑን  አስታውሰዋል።

በዚህም ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ተለዋዋጭ የሰላም ሁኔታዎች ባልተረጋገጡበት ወቅት ይህ ውጤት መመዝገቡ የሚበረታታ መሆኑንም በመግለጫቸው አብራርተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የተቋሙን የሪፎርም ስራዎችን ማጠናቀቅ፣ ዲጂታላይዝ አገልግሎቶችን በሁሉም መስክ ተደራሽ ማድረግ፣ የተሽከርካሪ የመጫን አቅም መጨመር ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

እንዲሁም የመርከቦችን ብዛት በቁጥር መጨመርና ተጨማሪ የኮንቴነር ግዢ መፈጸም በቀጣይ በጀት ዓመት የሚከናወኑ ተግባራት ስለመሆናቸው አብራርተዋል።        

 

                

 

       

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም