ቀጥታ፡

የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የተከበረው የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል በዓለ-ንግስ ያለአንዳች የፀጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የጋራ ፀጥታ ግብረ-ኃይል ገለጸ።

በዓሉ በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምሥራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የድሬዳዋ ፖሊስ፣ የምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ፖሊስ፣ የሐረሪ ክልል ፖሊስ፣ የምስራቅ እና ምዕራብ ኦሮሚያ እንዲሁም የሚሊሻ ኃይሉ ጋር የጋራ ዕቅድ በማውጣትና ከቤተክርስቲያኗ አባቶች ጋር በመምከር ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ግብረ-ኃይሉ ገልጿል፡፡

በዓሉን ለማክበር በመጡ ምዕመናን ላይ አንዳንድ የሞባይል ስርቆት ወንጀል በፈፀሙ አካላት ላይ በተቋቋመው ፈጣን ችሎት አማካኝነት ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር እስከ አንድ አመት ከስምንት ወር የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን የጋራ ፀጥታ ግብረ-ኃይሉ መግለጹን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም