ቀጥታ፡

የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአረኪዮሎጂ እና ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራ በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአረኪዮሎጂ እና ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራ በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ ተመዘገበ፡፡

በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 46ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ማዕከል ዓመታዊ ጉባዔ የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአረኪዮሎጂ እና ፓሊዮንቶሎጂ ሥፍራ ሶስት መስፈርቶችን በማሟላት የዓለም ቅርስ ሆነ ተመዝግቧል፡፡

ሥፍራውን በዓለም ቅርስነት ያበቁት መስፈርቶች፦

ከ2.5 ሚሊየን ዓመት እስከ መጨረሻው የድንጋይ ዘመን የሰው ልጅ ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ መገልገያዎች ይዞ የሚገኝ በመሆኑ፡፡

እስከ 2.5 ሚሊየን ዓመት እድሜ ያላቸው የተለያዩ የሰውና የእንስሳት ቅሪተ አካሎች በብዛት የሚገኙበት በመሆኑ::

የሰው ልጅ ከድንጋይ የተለያዩ መገልገያዎችን/መሳሪያዎችን ይሰራ እንደ ነበር የሚያሳዩ ስምንት የባልጩትና ሌሎች የድንጋይ መሳሪያ ማምረቻ ሥፍራዎችን ይዞ የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡

የቱሪዝም ሚንስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ለጉባኤው በላኩት መልእክት ይህ ቅርስ የተመዘገበው ሉሲ የተገኘችበትን 50ኛ አመት በምናከብርበት ወቅት መሆኑ ለሀገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል::

በእርግጥም ሀገራችን ምድረ ቀደምት መሆኗን ለአለም ተጨማሪ ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል::

ይህ ቅርፅ ተጠብቆ እንዲቆይም የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል::

መልካ ቁንጡሬ ባልጪት ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጂራ በሚወስደው ጎዳና 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አዋሽ ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቋሚ የሚዳሰሱ ቅርሶች 12ኛው መሆኑንም የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም