የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በ2016 በጀት ዓመት ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በ2016 በጀት ዓመት ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በ2016 በጀት ዓመት ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ፤ በ2016 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።
ከዚህ አንጻር በ2016 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 70 ቢሊየን ለማትረፍ ታቅዶ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ተቋሙ 51 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን በማስታወስ አፈጻጸሙ ግን ከፍተኛ እመርታ በማሳየት 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም አክለዋል።