ግብርና ሚኒስቴር ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በብዛት ማሳተፍ የሚያስችል ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ግብርና ሚኒስቴር ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በብዛት ማሳተፍ የሚያስችል ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ
አዳማ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ግብርና ሚኒስቴር ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በብዛት ማሳተፍ የሚያስችል ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን በሚኒስቴሩ የእንስሳትና አሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፅጌረዳ ፍቃዱ ገለጹ።
የአምስት ዓመት የማርና የንብ ሀብት ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርና የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፅጌረዳ ፍቃዱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓመት ከ500 ሺህ ቶን በላይ ማር ማምረት የሚያስችል እምቅ አቅም አላት።
በ2014 ዓ.ም የማር ልማት ኢንሼቲቭ ተግባራዊ ማድረግ ስንጀመር 146 ሺህ ቶን የማር ምርት በዓመት አምርተን ነበር ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 276 ሺህ ቶን ማምረት ተችሏል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 473 ሺህ ቶን ማር ለማምረት ግብ የተቀመጠ ሲሆን ለዚህም 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ጥራቱን የጠበቀ ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ቀፎ ይሰራጫል ነው ያሉት።
የማር ምርት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና ለአርሶ አደሮች ገቢ ማግኛ ምንጭ እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የዛሬው መድረክ ዓላማም በንብ ማነብ ሥራ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባለድርሻ አካላትን በስፋት ለማሳተፍና የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
ከሚኒስቴሩ ጋር ከሚሰሩ ባለድረሻ አካላት መካከል አንዱ ዓለም አቀፍ 'ኢንሴክት ፊዚዮሎጂና ኢኮሎጂ' ማዕከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከሉ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ እንደገለጹት በቀጣይ አምስት ዓመታት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶችን በማር ልማት ለማሰማራት 80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን አስታውቀዋል።
ገንዘቡ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን መገኘቱን ገልጸው፣ በፕሮግራሙ 80 በመቶ የሚሆኑ የገጠር ሴት ወጣቶች በስፋት በማር ልማት እንዲሳተፉ በማድረግ የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።
በፕሮግራሙ የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እና በገበያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የክህሎት፣ የኢንተርፕርነርሽፕና የገበያ ስልጠና ለወጣቶች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በዚህም የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያን በማር ምርት ተደራሽና ተወዳዳሪ ለማድረግ በምርት ጥራትና ብዛት ላይ የሚሰራውን ስራ ይደግፋል ብለዋል።
በተጨማሪም የማር አምራች የእሴት ሰንሰለት ለማሳደግ፣ የማር ምርት ጥራትና የማር አልሚ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ለማጠናከር ከሚኒስቴሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ነው ያሉት።
ፕሮግራሙ በ11 ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
አዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች የመጡና በማር ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አጋር አካላት ተሳትፈዋል።