ቀጥታ፡

በፓሪስ ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ለሚሮጠው ኤርሚያስ ይርጋ ሽኝት ተደረገለት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሻምበል አበበ ቢቂላን ፈለግ በመከተል በኦሎምፒክ መድረክ በባዶ እግሩ ለሚሮጠው ኤርሚያስ ይርጋ ሽኝት አድርጎለታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በሽኝቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በሮም ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ካደረጉ የኦሎምፒክ ጀግኖች መካከል ቀዳሚው አበበ ቢቂላ ነው።

የእሱን አርአያነት በመከተል በባዶ እግር በመሮጥ የሀገርን ስም ለማስጠራት እና ሻምበል አበበ ቢቂላን በሚያስታውስ መንገድ ለመሮጥ ወደ ፓሪስ በሚደረገው ጉዞ እንዲቀናውና በድል እንዲመለስም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

በአለም አደባባይ በባዶ እግር በመሮጥ ኦሎምፒክ ያሸነፈ ብቸኛው አፍሪካዊ ብሎም ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላን ገድል መዘከር የሁሉም ትውልድ ሃላፊነት እንደሆነ የገለፁት የስፖርት ዘረፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ናቸው።

በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬም በባዶ እግር መሮጥ እንደሚቻል እና የቀደምት ጀግና ታሪክን ይዞ ለማስቀጠል ወደ ፓሪስ በማቅናት በባዶ እግሩ ለሚሮጠው ኤርሚያስ ይርጋ ክብር ይገባዋል ብለዋል።

የቀድሞ ሞተር ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤሪሚያስ ይርጋ በበኩሉ በሮም፣ በአቴንስ፣ በደቡብ ኮሪያና በእንግሊዝ በተካሄዱ ኦሎምፒኮች ላይ በባዶ እግር በመሮጥ ሻምበል አበበ ቢቂላን ማስታወስ እንደቻለ መግለፁን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም