ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል አካታችና አሳታፊ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዳማ ፤ ሀምሌ 19/2016(ኢዜአ)፡- አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል አካታችና አሳታፊ ባደረገ መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ መሆኑን የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር አካል ጉዳተኞች በአገራዊ ምክክሩ ያላቸውን ተሳትፎና ሚና ለማጠናከር ያለመ ውይይት ዛሬ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ አገራዊ ምክክሩን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል ባካተተ መልኩ ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዚሁ ሲባል ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር መድረኩን ማዘጋጀቱን አንስተዋል።

ፌዴሬሽኑም አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ አጀንዳዎችን ቀድሞ ለምክክር ኮሚሽኑ ማቅረቡ የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይም ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍ በምክክር ሂደቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ አካል ጉዳተኞች በአገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ የማንቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

አገራዊ ምክክር በሚያመጣው ዘላቂ መፍትሔ ውስጥ አካል ጉዳተኞች የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት።

አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የለውጥ ሀሳብ በማምጣት ረገድ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም