ቀጥታ፡

የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት የድርሻውን እየተወጣ ነው

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦  የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ   ለተለያዩ አልባሳት አገልገሎት የሚውሉ  ተኪ ምርቶችን በማምረት  ከውጭ የሚገባን  ለማሰቀረት  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን  የፋብሪካው   ዋና ስራ አስኪያጅ   አስታወቁ።

ፋብሪካው ለአንድ ሺህ 200 ሠራተኞች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ መንግስቱ አረጋ እንዳሉት፤  ፋብሪካው ቀደም ሲል ኪሳራ ውስጥ ገብቶ የነበረበትን  አሰራር ለይቶ በማሻሻል  አመርቂ የማምረት ደረጃ ላይ ይገኛል።

በዚህም 90 በመቶ የሃገር ውስጥ የጥጥ ምርት በግብዓትነት በመጠቀም የማምረት ስራውን መቀጠሉን ለኢዜአ ተናግረዋል።።

በዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ ከጥጥ የተሰሩ አንሶላና የተለያዩ አልባሳትን በጣቃና ያለቀላቸውን ተኪ ምርቶች በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ  እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከፖሊስተር የሚመረቱ ክሮችን በማምረት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት  በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ፋብሪካው እያደረገው ባለው የማምረት እንቅስቃሴ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አሰረድተዋል።

በዚሁ ጥረትም አገራዊ ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ፕሮግራም ተሸላሚ መሆን እንደቻለም ጠቅሰዋል።

ጨርቃጨርቅ ፋብሪካው ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሜትር የአልባሳት   ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት በተደረገ የስራ እንቅስቃሴም 114 ሚሊዮን ብር የምርት ሽያጭ ማከናወኑን አስረድተዋል።

 ከዚህም  81 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 600 ሚሊዮን ብር ድረስ ሽያጭ ለመፈጸም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋብሪካው ለአንድ ሺህ 200 ሠራተኞችን የስራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አመልክተዋል።

ፋብሪካው አካባቢያዊ ብክለተን ለመጠበቅም ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ማስወገጃ /ትሪትመንት/ ገንብቶ እየተጠቀመ እንደሆነም ገልጸዋል።


 

በፋብሪካው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል  አቶ አዲሱ መኮንን በሰጡት አስተያየት፤ ፋብሪካው የሠራተኛውን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያተጋ ነፃ ህክምናን ጨምሮ   የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም  በማመቻቸት  እየደገፋቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

ስራቸውን በአግባቡ በማከናወን  ድርጅቱም መብትና ጥቅማቸውን እያከበረላቸው ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ገበያነሽ አረጋው ናቸው።

የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ  ከተቋቋመ ከ60 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም