ቀጥታ፡

በክልሉ ከ207 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ ጤፍ እየተሰበሰበ ነው 

ሮቤ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በበልግ አዝመራ ከ207 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ የጤፍ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በምሥራቅ ባሌ ዞን በመካናይዜሽን ታግዞ እየተሰበሰበ የሚገኘውን የጤፍ ሰብል በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል። 

በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በበልግ አዝመራ የለማ ከ207 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ ጤፍ እየተሰበሰበ ነው። 


 

የጤፍ ሰብሉ የለማው በባሌና ምስራቅ ባሌ ዞኖች እንዲሁም በሌሎች በልግ አብቃይ የክልሉ አካባቢዎች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ የምሥራቅ ባሌ ዞን ከክልሉ በልግ አብቃይ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን የእዚህ አካባቢ የበልግ ወቅትም ከግንቦት መጀመሪያ እስከ ሀምሌ መጨረሻ መሆኑን አንስተዋል።

የምሥራቅ ባሌ ዞን አርሶ አደሮችም ዘንድሮ በበልግ አዝመራ ያለሙትን ጤፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምባይነር ተጠቅመው ምርት እየሰበሰቡ ሲሆን ይህም ለሌችም አካባቢዎች በተሞክሮነት የሚወሰድ እንደሆነ ገልጸዋል። 

አቶ ሙስጠፋ እንዳሉት በክልሉ እስከ አሁን በተደረገው ጥረት በበልጉ ወቅት በጤፍ ሰብል ከለማው ከ207 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል። 

ሰብልን በቴክኖሎጂ ታግዞ መሰብሰብ ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ከማስቀረቱም በላይ ጥራቱ የተጠበቀ ምርት በጊዜ ሰብስቦ ለገበያ ለማቅረብ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አክለዋል።

በምሥራቅ ባሌ ዞን የደረሰ ሰብልን ከኮምባይነር በተጨማሪ በጥቃቅን መሽኖችና በሰው ጉልበት የመሰብሰቡ ሥራም ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሰብሪያ አብዱቄ ገልጸዋል። 


 

በዞኑ በበልጉ ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች ከለማው 152 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 18 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በጤፍ የለማ መሆኑን አመልክተዋል። 

ከከምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል በከር አህመድ፣ በበልግ አዝመራ ያለሙትን የጤፍ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ይደርስ የነበረውን ብክነት በማስቀረት ከአንድ ሄክታር 28 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል። 

በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበልግ ምርት ወቅት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም