ኢትዮጵያና ኦሊምፒክ ከገረመው ደንቦባ እስከ ሰለሞን ባረጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኦሊምፒክ ከገረመው ደንቦባ እስከ ሰለሞን ባረጋ

(በሙሴ መለሰ)
እንደ መነሻ
የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን መነሻ ለማወቅ 3 ሺህ ዓመት ወደ ኋላ መለስ ማለት ያስፈልጋል። በጽሁፍ የሰፈሩ የታሪክ ድርሳናት የኦሊምፒክ ጽንሰ ሀሳብ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ776 ዓመተ ዓለም በግሪክ እንደሆነ ይገልጻሉ። በወቅቱ “የኦሊምፒክ የውልደት ስፍራ” ተብላ በምትጠራው በጥንታዊቷ ግሪክ ፔሎፖኒስ ግዛት በምትገኘው ኦሊምፒያ ከተማ የተለያዩ የስፖርታዊ ሁነቶች መድረክ በየአራት ዓመቱ ይካሄድ ነበር። ውድድሩ “ኦሊምፒያድ” በሚል ስያሜ ይካሄድ የነበረ ሲሆን ስፖርታዊ ሁነቱ ጥንታዊ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተብሎ ይጠራ ነበር።
ዘመናዊ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ የተጀመረው እ.አ.አ በ1894 የሶርበን ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩት ፈረንሳዊው ፔዬር ደ ኩበርቲን ነበር። በዚው ዓመት በተደረገ ስብሰባ አቴንስ ላይ የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንዲጀመር ተወሰነ።
ግሪክ እ.አ.አ በ1986 የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያስተናጋደች ሲሆን በውድደሩ ላይ 14 ሀገራት ተካፋይ ነበሩ። አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቺሊ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ታላቋ ብሪታኒያ (አየርላንድን ጨምሮ)፣ ግሪክ፣ ሀንጋሪ፣ ጣልያን፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድና አሜሪካ በውድድሩ የተሳተፉ ሀገራት ናቸው።
በመጀመሪያው ታሪካዊ ሁነት ከስፖርተኞች በተጨማሪ ሰዓሊዎችና መሃንዲሶች የተለያዩ ስራዎችን አቅርበው ተወዳድረዋል። በዚህም ኦሊምፒክ የስፖርት ብቻ ሳይሆን የባህል መድረክ እንደሆነ ማሳያ መሆኑ በወቅቱ ይገለጽ ነበር።
16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎችና የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ታሪካዊ ተሳትፎ
የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ1896 ቢጀመርም ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ 60 ዓመታትን ጠብቃለች። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በውደሩ የተሳተፋቸው በአውስትራሊያ ሜልቦርን እ.አ.አ በ1956 በተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነው። በውድድሩ ከ72 ሀገራት የተውጣጡ 3 ሺህ 314 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያም በታሪካዊ ተሳትፎዋ 12 ስፖርተኞችን ይዛ ቀርባለች። በወንዶች 100፣ 200፣ 400፣ 4 በ100 ዱላ ቅብብል፣ 800 እና 1 ሺህ 500፣ ማራቶንና ብስክሌት ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። አበበ ኃይሉ፣ በየነ ለገሰ፣ ሮባ ንጉሴ፣ አጃነው በየነ፣ ማሞ ወልዴ፣ በቀለ ኃይሌ፣ ባሻይ ፈለቀና ገብሬ ብርቃይ በውድድሩ በአትሌቲክስ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
ታዋቂው አትሌት ማሞ ወልዴ በ800፣ 1 ሺህ 500 ሜትር እና 4 በ100 ዱላ ቅብብል ላይ ቢሳተፍም ከማጣሪያው ማለፍ አልቻለም። በማራቶን የተወዳዳሩት ባሻይ ፈለቀና ገብሬ ብርቃይ 29ኛ እና 32ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ገረመው ደንቦባ፣ መስፍን ተስፋዬ፣ ዘሃይ ባህታና ንጉሴ መንግስቱ በብስክሌት ላይ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች ነበሩ።
በቡድን የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድር የተካፈሉት ገረመው ደንቦባ፣ መስፍን ተስፋዬና ዘሃይ ባህታ 99 ነጥቦችን በማግኘት 9ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በነጠላ የብስክሌት ውድድር ገረመው ደንቦባ 25ኛ፣ መስፍን ተስፋዬ 36ኛ እና ዛሃይ ባህታ 38 ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል። ንጉሴ መንግስቱ ውድድሩን ባለማጠናቀቁ ደረጃው ውስጥ አልገባም።
ታዋቂው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍና ሰንደቅ አለማዋን በኦሊምፒክ ስፖርት በመያዝ ቀዳሚው አትሌት ነበር። አንጋፋው ብስክሌተኛ የካቲት ወር 2015 ዓ.ም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ90 ዓመቱ ሕይወቱ ማላፉ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ምንም ሜዳሊያ ባለመግኘቷ ደረጃ ውስጥ አልገባችም።
የአበበ ቢቂላ የባዶ እግር ውቅር
ከ83 ሀገራት የተወጣጡ 5 ሺህ 347 ስፖርተኞች በተሳተፉበት በጣልያን ሮም ከተማ እ.አ.አ በ1960 በተካሄደው 17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ10 ስፖርተኞች በአትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርት ተወዳድራለች።
በወንዶች ማራቶን አትሌት አበበ በቂላ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ። አትሌት አበበ የወርቅ ሜዳሊያውን ያገኘው በባዶ እግሩ ሮጦ መሆኑን ታሪካዊ ገድሉን ይበልጥ ደማቅ ያደርገዋል።
አትሌቱ ለኢትዮጵያ በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ሜዳሊያ ከማግኘት ባሻገር በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ወርቅ ያገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት በመሆን ታሪክ ሰርቷል።
አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ለምን በባዶ እግሩ እንደሮጠ ሲጠየቅ “ምንጊዜም በፅናትና በጀግንነት ታግላ የምታሸንፈውን ኢትዮጵያ ሀገሬን አለም አጥብቆ እንዲያውቃት ስለምፈልግ ነው” ሲል በወቅቱ ምላሽ ሰጥቷል።
ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎዋ ወቅት የነበሩት ሮባ ንጉሴ፣ ገረመው ደንቦባና ንጉሴ መንግስቱ በ17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይም ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ በአበበ በቂላ አማካኝነት ባገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ 21ኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቃለች።
የአበበ ዳግም ድምቀት በቶኪዮ
ቶኪዮ እ.አ.አ በ1964 18ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካሄደባት ከተማ ናት። ኢትዮጵያም በውድድሩ በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት ስፖርቶች 12 አትሌቶችን አሳትፋለች። ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት በኦሊምፒክ ስትሳተፍ የቶኪዮው የመጀመሪያው ነው።
አትሌት አበበ ቢቂላ በወንዶች ማራቶን 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ በማሸነፍ ለኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ስፖርት ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። አትሌት አበበ በሁለት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ አትሌት በመሆን ድርብ ታሪክ ሰርቷል። ኢትዮጵያ በውድድሩ 1 የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ በማግኘት 24ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
አትሌት ማሞ ወልዴና የሜክሲኮ ታሪካዊ ድሎች
19ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካሄደው እ.አ.አ በ1968 በሜክሲኮ መዲና ሜክሲኮ ከተማ አዘጋጅነት ነው። ኢትዮጵያ በ18 ስፖርተኞች በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት የስፖርት አይነቶች ተሳትፋለች። በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ በአጭርና መካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ የሮጠው አትሌት ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ በነበረው ውድድር ውጤታማ መሆን ችሏል።
አትሌት ማሞ በወንዶች ማራቶን 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል። በተጨማሪም በ10 ሺህ ሜትር ኬንያዊውን አትሌት ናቢባ ናፍታሊ ቴሙን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
አትሌት ማሞ በአንድ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ሁለት ሜዳሊያ ያስገኘ የመጀመሪያው አትሌት ሆኗል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ ተሳትፎዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሜዳሊያ በላይ ማግኘት ችላለች። 112 ሀገራት በተሳተፉበት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 2 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 25ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ 31 አትሌቶችን ያሳተፈችበት 20ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች
በጀርመን ሙኒክ ከተማ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ1972 በተካሄደው 20ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከ121 ሀገራት የተወጣጡ 7 ሺህ 134 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። በውድድሩ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት 31 ስፖርተኞችን ይዛ ቀርባለች።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ በወንዶች በ100፣ 800፣ 1500፣ 5000፣ 10000 ሜትር እና 4 በ100 ዱላ ቅብብል ተሳትፋለች። አትሌት ማሞ ወልዴ በሶስተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎው በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።
በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር 3ኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል። መሐመድ አየለና ፍቃዱ ገብረስላሴ ኢትዮጵያን ወክለው በቦክስ ስፖርት የተወዳደሩ አትሌቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ በአምስተኛው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ በ2 የነሐስ ሜዳሊያዎች ከ121 ሀገራት 41ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
የማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር ገድል በሞስኮ
የሩሲያ መዲና ሞስኮ እ.አ.አ በ1980 የተካሄደው 22ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ደጋሽ ነበረች። ከ80 ሀገራት የተወጣጡ 5 ሺህ 256 ተወዳዳሪዎች በስፖርት ድግሱ ላይ ታድመዋል። ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት ስፖርቶች 45 ተወዳዳሪዎችን አሳትፋለች።
ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች በአስደናቂ ብቃት በማሸነፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። ምሩጽ በአንድ ኦሊምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል።
አትሌቱ በሙኒክ በተካሄደው 20ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቶ ነበር። ከምሩጽ በተጨማሪ አትሌት መሐመድ ከድር በ10 ሺህ ሜትር እና ሻምበል እሸቱ ቱራ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል።
በሞስኮ በተካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት አትሌቶችን አሳትፋለች። ፋንታዬ ሲራክ በ800 እንዲሁም አምሳል ወልደገብርኤል በ1 ሺህ 500 ሜትር አገራቸውን ወክለው ተወዳድረዋል። ሁለቱም አትሌቶች በተወዳደሩባቸው ርቀቶች ከመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ኢትዮጵያ በ2 ወርቅና በ2 የነሐስ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 17ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 17ኛ ደረጃ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ታሪክ ትልቁን ደረጃ ያገኘችበት ውድድር ነው።
ታሪክ ሰሪዋ ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና
ኢትዮጵያ 7ኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ያደረገችው እ.አ.አ በ1992 በስፔን ባርሴሎና በተካሄደው 25ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነው። በስፖርታዊ ሁነቱ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና በብስክሌት 20 ስፖርተኞችን አሳትፋለች።
አትሌት ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺህ ሜትር 31 ደቂቃ ከ6 ሴኮንድ ከ2 ማይክሮ ሴኮንድ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። ደራርቱ በውድድሩ ከደቡብ አፍሪካዋ አትሌት ኤላና ሜየር ጋር በመጨረሻው 400 ሜትር ያደረጉት ፉክክር ልብ እንጠልጣይ የሚባል ነበር።
ደራርቱ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ ወርቅ ያመጣች የመጀመሪያ ሴት አትሌት ሆናለች በተጨማሪም በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ ያገኘች አፍሪካዊ አትሌትም መሆን ችላለች።
በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች አዲስ አበበ፣ በ5000 ሜትር ወንዶች ፊጣ ባይሳ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። ኢትዮጵያ በ1 የወርቅና 2 የነሐስ በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከ169 ሀገራት 33ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ኦሊምፒክ
26ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካሄዳው በአሜሪካ አትላንታ እ.አ.አ በ1996 ሲሆን ኢትዮጵያ 18 ስፖርተኞችን በአትሌቲክስና ቦክስ ስፖርቶች አሳትፋለች።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በ10 ሺህ ሜትር 27 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ ከ34 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በርቀቱም የኦሊምፒክ ክብረወሰንን አሻሽሏል። በወቅቱ ኃይሌ ከኬንያዊው አትሌት ጋር ውድድሩን ለማሸነፍ ያደረገው ትንቅንቅ ከኢትዮጵያውያን ጭንቅላት የሚጠፋ አይደለም።
በሴቶች ማራቶን አትሌት ፋጡማ ሮባ 2 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ውድድሩን በማሸነፍ ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። ፋጡማ በሴቶች ማራቶን ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣች የመጀመሪያዋ አትሌት ናት።
በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት ጌጤ ዋሚ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ጥበቡ ቢሆነኝና ያሬድ ወልደሚካኤል በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በቦክስ ስፖርት የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች ናቸው። ኢትዮጵያ በ2 የወርቅና 1 የነሐስ በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 34ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ4 ወርቅ የደመቀችበት የሲድኒ ኦሊምፒክ
የአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ 27ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ2000 ያዘጋጀች ሲሆን ከ199 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 647 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ቦክስ 26 ተወዳዳሪዎችን አሳትፋለች።
በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። ኃይሌ በ26ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት ወርቅ አግኝቶ ነበር። በዚህም ኃይሌ ከአበበ ቢቂላ በኋላ በሁለት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል።
አትሌት ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺህ ሜትር አሸንፋለች። ደራርቱ ከ4 ዓመት በፊት በነበረው ውድድር በተመሳሰይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው። ደራርቱ በሁለት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት አትሌት በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርታለች።
በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሚሊዮን ወልዴ እንዲሁም አትሌት ገዛኸኝ አበራ በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተዋል። አትሌት ገዛኸኝ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ በወንዶች ማራቶን ወርቅ ያመጣ የመጀመሪያው አትሌት ነው።
አትሌት ጌጤ ዋሚ በ10 ሺህ ሜትር የብርና በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም አትሌት አሰፋ መዝገቡ በ10 ሺህ ሜትር እና ተስፋዬ ቶላ በወንዶች ማራቶን በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።
ዮሐንስ ሽፈራውና አዲሱ ጥበቡ በቦክስ ስፖርት ኢትዮጵያን ወክለው ቢሳተፉም ከመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ማለፍ አልቻሉም። ሌላኛው ፀጋስላሴ አረጋዊ ለውድድሩ ወደ ሲዲኒ ቢያቀናም ምንም ጨዋታ ሳያደርግ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ 4 የወርቅ፣ 1 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 20ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከኦሊምፒክ ጋር የተዋወቀበት ውድድር
የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካሄደበት ታሪካዊቷ የግሪክ ከተማ አቴንስ እ.አ.አ በ2004 የተካሄደውን 28ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አስተናግዳለች። በውድድሩ ላይ ከ201 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 557 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ቦክስ 26 ስፖርተኞችን አሳትፋለች።
በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች 27 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በርቀቱ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን አሻሽሏል። በውድድሩ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ስለሺ ስህን የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። ቀነኒሳ በ5 ሺህ ሜትር በሞሮኮዋዊው አትሌት ሂሻም ኤል ግሩዥ ተቀድሞ የብር ሜዳሊያ አገኝቷል።
አትሌት መሰረት ደፋር 14 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ከ65 ማይክሮ ሴኮንድ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። አትሌት መሰረት በርቀቱ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች የመጀመሪያ ሴት አትሌት ናት። በውድድሩ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች። በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ የብር እና አትሌት ደራርቱ ቱሉ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ በ2 የወርቅ፣ 3 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 28ኛ ደረጃን በማግኘት በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።
አረንጓዴው ጎርፍ በቤጂንግ ሰማይ ስር
የ29ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች መዳረሻ የቻይናዋ መዲና ቤጂንግ ናት። ውድድሩ የተካሄደው እ.አ.አ በ2008 ነበር። በታላቁ የስፖርት መድረክ ከ204 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 899 አትሌቶች ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ 27 ተወዳዳሪዎችን ይዛ በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ተሳትፎ አድርጋለች።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ወንዶች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በድል ያሸበረቀ ውድድር አሳልፏል። አትሌት ቀነኒሳ ከምሩጽ ይፍጠር የሞስኮ ገድል በኋላ በሁለቱ ርቀቶች ወርቅ ያገኘ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል።
በኦሊምፒክ ሁለተኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አኩሪ ድል አስመዝግባለች። አትሌት ጥሩነሽ በኦሊምፒክ በሁለቱ ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርታለች።
አትሌት ስለሺ ስህን በ10 ሺህ ሜትር እና አትሌት መሰረት ደፋር የብር ሜዳሊያዎችን ያገኙ ሲሆን አትሌት ፀጋዬ ከበደ በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስመዝግቧል።
ኢትዮጵያ በ4 የወርቅ፣ 2 የብርና 1 የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከ204 ሀገራት 18ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ሴት አትሌቶች ብቻ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙበት መድረክ
እ.አ.አ በ2012 በእንግሊዝ ለንደን የተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በውድድሩ 12ኛ ተሳትፎዋን ያደረገችበት ነበር። ኢትዮጵያ በስፖርታዊ ሁነቱ 35 ስፖርተኞችን በአትሌቲክስና በውሃ ዋና ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ አሳትፋለች።
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በሶስተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች። አትሌት ጥሩነሽ ከደራርቱ ቱሉ በኋላ በሁለት ተከታታይ ውድድሮች በተመሳሳይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሁለተኛ ሴት አትሌት ሆናለች። ጥሩነሽ በ500 ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።
በሴቶች 5 ሺህ ሜትር አትሌት መሰረት ደፋር የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። አቴንስ ላይ በተካሄደው 28ኛው የኢሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታ ነበር።
አትሌት ቲኪ ገላና በሴቶች ማራቶን አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቃለች። አትሌት ቲኪ ከአትሌት ፋጡማ ሮባ በኋላ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሁለተኛ ሴት አትሌት ሆናለች።
አትሌት ደጀን ገብረመስቀል በ5000 ሜትር ወንዶችና አትሌት ሶፊያ አሰፋ በ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።
የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ታናሽ ወንድም አትሌት ታሪኩ በቀለ በ10000 ሜትር ወንዶች እና አትሌት አበባ አረጋዊ በ1500 ሜትር ሴቶች በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
የዓለም ውሃ ስፖርት የበላይ አካል ‘ወርልድ አኳቲክ’ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የውሃ ዋና ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ በሰጠው ዓለም አቀፍ የውድድር እድል አማራጭ በወንዶች ሙሉዓለም ግርማ እና በሴቶች ያኔት ስዩም ባደረጉት የማጣሪያ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ አልቻሉም።
ኢትዮጵያ በውድድሩ በ3 የወርቅ፣ 2 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 24ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አንድ ወርቅ ብቻ የተገኘበት ኦሊምፒክ
የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል የባህር ጠረፍ ከተማ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እ.አ.አ በ2016 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጅ ከተማ። በውድድሩ ላይ ከ205 ሀገራት የተወጣጡ 11 ሺህ 180 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። ከሀገራቱ በተጨማሪም በኦሊምፒክ ባንዲራ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የስደተኞች የኦሊምፒክ ቡድን ተወዳዳሪዎች ተካፍለዋል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ ብስክሌትና ውሃና ዋና ስፖርቶች ተሳትፋለች። የረጅም ርቀት ሯጯ አትሌት አልማዝ አያና በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች 29 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ ከ45 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ በውድድሩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። አትሌት አልማዝ በወቅቱ የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ሰብራለች። በተጨማሪም አትሌቷ በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በወንዶች ማራቶንና አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ1 ሺህ 500 ሜትር በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።
አትሌት ታምራት ቶላ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች፣ አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች እና አትሌት ማሬ ዲባባ በሴቶች ማራቶን በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።
በብስክሌት የወንዶች የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያ ወክሎ የተወዳደረው ጽጋቡ ግርማይ ውድድሩን ሳይጨርስ አቋርጧል።
በውሃ ዋና በወንድ ሮቤል ኪሮስ በወንዶች 100 ሜትር ነጻ ቀዘፋ እንዲሁም ራሔል ገብረስላሴ በሴቶች 50 ሜትር ነጻ ቀዘፋ የማጣሪያ ውድድር ተሳትፈው ከመጀመሪያው ዙር ማለፍ አልቻሉም።
ኢትዮጵያ በውድድሩ በ1 የወርቅ፣ 2 የብርና 5 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 44ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ዝቅተኛ ደረጃን ያገኘችበት ውድድር
32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካሄደው ከ4 ዓመት በፊት በጃፓን ቶኪዮ ነበር። በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 204 ሀገራት ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ በ4 ስፖርቶች 38 ስፖርተኞችን አሳትፋለች። ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋናና ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ ቴኳንዶ ተሳትፋለች።
በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ሰለሞን ባረጋ 27 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ22 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች አትሌት ለሜቻ ግርማ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች እና አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በብስክሌት በሴቶች የጎዳና ላይ ውድድር ሰላም አምሃ የተሳተፈች ቢሆንም ውድድሩን ሳታጠናቅቅ ቀርታለች።
በውሃ ዋና ስፖርት የተወዳደረው አብደልማሊክ ሙክታር በ50 ሜትር ነጻ ቀዘፋ ማጣሪያ ከመጀመሪያው ዙር ማለፍ አልቻለም።
በወርልድ ቴኳንዶ የተወዳደረው ሰለሞን ቱፋ በ58 ኪሎ ግራም ወንዶች የጥሎ ማለፍ ዙር ጃፓናዊውን ሰርጂዮ ሱዙኪን አሸንፎ ሩብ ፍጻሜ ቢገባም 8 ውስጥ በቱኒዚያዊው መሐመድ ካሊሊ ጄንዱቢ ተሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አላለፈም።
ኢትዮጵያ 1 የወርቅ፣ 1 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 56ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ ያጠናቀቀችበት ደረጃ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ታሪክ ዝቅተኛው ነው።
ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸው 3 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1976 በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው 21ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ እ.አ.አ በ1984 በተከናወነው 23ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እና በኮሪታ ሪፐብሊክ ሴኡል እ.አ.አ በ1988 በተሰናዳው 24ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ አልተሳተፈችም።
ኢትዮጵያ በሶስቱም ውድድሮች ላይ ያልተሳተፈችው “በፖለቲካዊ ምክንያቶች በነበራት አቋም” እንደሆነ የተለያዩ ጽሁፎች ያመለክታሉ።
58 ሜዳሊያዎች በ14 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች
ኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በ14 ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
በዚህም ተሳትፎዋ 23 የወርቅ፣ 12 የብር እና 23 የነሐስ በአጠቃላይ 58 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። ሁሉም ሜዳሊያዎች የተገኙት በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ነው። 36 አትሌቶች 58ቱን ሜዳሊያዎች አስገኝተዋል።
ዘንድሮስ?
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 206 ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ።
ኢትዮጵያ በ15ኛ የውድድሩ ተሳትፎዋ አትሌቲክስና ውሃ ዋና ስፖርቶች 38 ስፖርተኞችን ታሳትፋለች።
ቀነኒሳ በቀለ፣ ሰለሞን ባረጋና በሪሁ አረጋዊ በወንዶች፣ ጉዳፍ ፀጋይ፣ ትዕግስት አሰፋና አትሌት ፅጌ ዱጉማ በሴቶች በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ወክለው ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መንግስት ሽኝት ተደርጎለታል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሽኝቱ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት አትሌቶች በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከምንም በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሀገራቸውን ስኬታማ ለማድረግ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አትሌቶች ሀገርን ከማስጠራት ጎን ለጎን በስፖርታዊ ጨዋነት ውድድራቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅሪበዋል።
በተያያዘም የቱሪዝም ሚኒስቴር በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሐምሌ 16 ቀን የሽኝት መርሐ ግብር አካሂዷል።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በኦሊምፒኩ የሚሳተፉ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና የቱሪዝም ሀብቶች ለዓለም እንዲያስተዋዉቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያን ወክለው በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ውጤት ታስመዘግብ ይሆን? ለ17 ቀናት የሚቆየው ውድድር ምላሽ አለው።